ምዕራፍ 14።

1፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል፥ ብዝበዛሽንም በውስጥሽ ይካፈላሉ።

2፤ አሕዛብንም ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ ለሰልፍ እሰበስባለሁ፤ ከተማይቱም ትያዛለች፥ ቤቶችም ይበዘበዛሉ፥ ሴቶችም ይነወራሉ፤ የከተማይቱም እኵሌታ ለምርኮ ይወጣል፥ የቀረው ሕዝብ ግን ከከተማ አይጠፋም።

3፤ እግዚአብሔርም ይወጣል፥ በሰልፍም ቀን እንደ ተዋጋ ከእነዚያ አሕዛብ ጋር ይዋጋል።

4፤ በዚያም ቀን እግሮቹ በኢየሩሳሌም ትይዩ በምሥራቅ በኩል ባለው በደብረ ዘይት ላይ ይቆማሉ፤ ደብረ ዘይትም በመካከል ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ይሰነጠቃል፥ እጅግም ታላቅ ሸለቆ ይሆናል፤ የተራራውም እኵሌታ ወደ ሰሜን፥ እኵሌታውም ወደ ደቡብ ይርቃል።

5፤ የተራሮችም ሸለቆ እስከ አጸል ይደርሳልና በተራሮች ሸለቆ ትሸሻላችሁ፤ በይሁዳም ንጉሥ በዖዝያን ዘመን ከሆነው ከምድር መናወጥ ፊት እንደ ሸሻችሁ ትሸሻላችሁ፤ አምላኬ እግዚአብሔርም ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ይመጣል።

6፤ በዚያም ቀን በረዶና ውርጭ እንጂ ብርሃን አይሆንም።

7፤ አንድ ቀንም ይሆናል፥ እርሱም በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ይሆናል፤ ቀንም አይሆንም፥ ሌሊትም አይሆንም፤ ሲመሽም ብርሃን ይሆናል።

8፤ በዚያም ቀን የሕይወት ውኃ ከኢየሩሳሌም ይወጣል፤ እኵሌታው ወደ ምሥራቁ ባሕር፥ እኵሌታውም ወደ ምዕራቡ ባሕር ይሄዳል፤ ይህ በበጋና በክረምት ይሆናል።

9፤ እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል፤ በዚያ ቀን እግዚአብሔር አንድ፥ ስሙም አንድ ይሆናል።

10፤ ምድር ሁሉ ከጌባ ጀምሮ በኢየሩሳሌምም ደቡብ በኩል እስካለችው እስከ ሬሞን ድረስ ተለውጣ እንደ ዓረባ ትሆናለች፤ እርስዋም ከፍ ከፍ ትላለች፥ ከብንያምም በር ጀምሮ እስከ ፊተኛው በር ስፍራ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ፥ ከሐናንኤልም ግንብ ጀምሮ እስከ ንጉሡ መጥመቂያ ድረስ በስፍራዋ ትኖራለች።

11፤ ሰዎችም ይኖሩባታል፥ ከዚያም ወዲያ እርግማን አይሆንም፤ ኢየሩሳሌምም ተዘልላ ትኖራለች።

12፤ እግዚአብሔርም ከኢየሩሳሌም ጋር የተዋጉትን አሕዛብ ሁሉ የሚቀሥፍበት ቸነፈር ይህ ነው፤ በእግራቸው ሲቆሙ ሥጋቸው ይበሰብሳል፥ ዓይኖቻቸውም በዓይነስባቸው ውስጥ ይበሰብሳሉ፥ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል።

13፤ በዚያም ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ ታላቅ ሽብር በእነርሱ ላይ ይሆናል፤ እያንዳንዱም የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፥ እጁም በባልንጀራው እጅ ላይ ይነሣል።

14፤ ይሁዳም ደግሞ በኢየሩሳሌም ውስጥ ሆኖ ይዋጋል፤ በዙሪያም ያሉት የአሕዛብ ሁሉ ሀብት እጅግ ብዙ ወርቅና ብር ልብስም ይሰበሰባል።

15፤ በፈረስና በበቅሎ፥ በግመልና በአህያ፥ በዚያም ሰፈር ባለ እንስሳ ሁሉ ላይ የሆነ ቸነፈር እንደዚያ ያለ ቸነፈር ይሆናል።

16፤ በኢየሩሳሌም ላይ ከመጡት ከአሕዛብ ሁሉ የቀሩት ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ፥ የዳስ በዓልንም ያከብሩ ዘንድ በየዓመቱ ይወጣሉ።

17፤ ከምድርም ወገኖች ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ለማይወጡ ለእነርሱ ዝናብ አይዘንብላቸውም።

18፤ የግብጽም ወገን ባይወጣ ወደዚያም ባይመጣ፥ እግዚአብሔር የዳስ በዓልን ያከብሩ ዘንድ የማይወጡትን አሕዛብ የሚቀሥፍበት ቸነፈር በእርሱ ላይ ይሆናል።

19፤ የግብጽ ቅጣት፥ የዳስ በዓልንም ያከብሩ ዘንድ የማይወጡት የአሕዛብ ሁሉ ቅጣት እንደዚህ ይሆናል።

20፤ በዚያ ቀን በፈረሶች ሻኵራ ላይ። ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ተብሎ ይጻፋል፤ በእግዚአብሔርም ቤት ያሉ ምንቸቶች በመሠዊያው ፊት እንዳሉ ዳካዎች ይሆናሉ።

21፤ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ምንቸቶችም ሁሉ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ ይሆናሉ፤ የሚሠዉትም ሰዎች ሁሉ ይመጣሉ ከእነዚያም ወስደው ይቀቅሉባቸዋል፤ በዚያም ቀን በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ቤት ከነዓናዊው ከእንግዲህ ወዲያ አይገኝም።