መዝሙር 98

የዳዊት መዝሙር።

1 ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን አመስግኑ፥ እግዚአብሔር ተኣምራትን አድርጎአልና፤ ቀኙ የተቀደሰም ክንዱ ለእርሱ ማዳን አደረገ።

2 እግዚአብሔር ማዳኑን አስታወቀ፥ በአሕዛብም ፊት ጽድቁን ገለጠ።

3 ለያዕቆብ ምሕረቱን ለእስራኤልም ቤት እውነቱን አሰበ፤ የምድር ዳርቻዎች ሁሉ የአምላካችንን ማዳን አዩ።

4 ምድር ሁሉ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር እልል በሉ፤ አመስግኑ፥ ደስ ይበላችሁ፥ ዘምሩም።

5 ለእግዚአብሔር በመሰንቆ፥ በመሰንቆና በዝማሬ ድምፅ ዘምሩ።

6 በዋሽንትና በመለከት ድምፅ በንጉሥ በእግዚአብሔር ፊት እልል በሉ።

7 ባሕርና ሞላዋ፥ ዓለምም በእርስዋም የሚኖሩ ይናወጡ።

8 ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ፤ ተራሮች ደስ ይበላቸው፥ በምድር ሊፈርድ ይመጣልና።

9 ለዓለምም በጽድቅ ለአሕዛብም በቅንነት ይፈርዳል።