መዝሙር 64

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ወደ አንተ በለመንሁ ጊዜ ጸሎቴን ስማኝ፥ ከጠላትም ፍርሃት ነፍሴን አድን።

2 ከክፉዎች ሸንጎ ከዓመፀኞችም ብዛት ሰውረኝ።

3 እንደ ሰይፍ ምላሳቸውን አሰሉ፤ መራራ ነገርን ለማድረግ፥

4 ንጹሕንም በስውር ለመንደፍ ቀስትን ገተሩ፤ ድንገት ይነድፉታል አይፈሩምም።

5 ለእነርሱ ለራሳቸው ክፉ ነገርን አጸኑ፤ ወጥመድን ይሰውሩ ዘንድ ተማከሩ፤ ማንስ ያየናል? ይላሉ።

6 ዓመፃን ፈልጓት፥ ሲፈትኑም አለቁ፤ የሰው የውስጥ አሳቡና ልቡ የጠለቀ ነው፥

7 እግዚአብሔርም ከፍ ከፍ ይላል። የድንገትም ፍላጻ፤ ያቈስላቸዋል፤

8 አንደበታቸው ያሰናክላቸዋል፥ የሚያዩአቸውም ሁሉ ይደነግጣሉ።

9 ሰዎች ሁሉ ፈሩ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ ተናገሩ፥ ሥራውንም አስተዋሉ።

10 ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፥ በእርሱም ይታመናል፤ ልባቸውም የቀና ሁሉ እልል ይላሉ።