መዝሙር 54

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ዜፋውያን መጥተው ለሳኦል። እነሆ ዳዊት በእኛ ዘንድ ተሸሽጓል ብለው በነገሩት ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት።

1 አቤቱ፥ በስምህ አድነኝ፥ በኃይልህም ፍረድልኝ።

2 አቤቱ፥ ጸሎቴን ስማኝ፥ የአፌንም ቃል አድምጥ፤

3 እንግዶች ቁመውብኛልና፥ ኃያላንም ነፍሴን ሽተዋታልና። እግዚአብሔርን በፊታቸው አላደረጉትም።

4 እነሆ፥ እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ ጌታዬም ለነፍሴ ደጋፊዋ ነው።

5 ክፋትን ወደ ጠላቶቼ ይመልሳታል፤ በእውነትህም አጥፋቸው።

6 ከፈቃዴ እሠዋልሃለሁ፤ አቤቱ፥ መልካም ነውና ስምህን አመሰግናለሁ፤

7 ከመከራ ሁሉ አድኖኛልና፥ ዓይኔም በጠላቶቼ ላይ አይታለችና።