መዝሙር 12

ለመዘምራን አለቃ፥ ስለ ስምንተኛ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ አድነኝ፤ ደግ ሰው አልቆአልና፥ ከሰው ልጆችም መተማመን ጐድሎአልና።

2 እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ።

3 የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል፥ ታላቅ ነገርን የምትናገረውን ምላስ፤

4 ምላሳችንን እናበረታለን፤ ከንፈራችን የእኛ ነው፥ ጌታችን ማን ነው? የሚሉትን።

5 ስለ ድሆች መከራ፥ ስለ ችግረኞች ጩኸት እግዚአብሔር። አሁን እነሣለሁ ይላል፤ መድኃኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ።

6 በምድር ላይ እንደ ተፈተነ ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ ብር። የእግዚአብሔር ቃላት የነጹ ቃላት ናቸው።

7 አቤቱ፥ አንተ ጠብቀን፥ ከዚህችም ትውልድ ለዘላለም ታደገን።

8 በሰው ልጆች ዘንድ ምናምንቴ ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ክፉዎች በዙሪያው ሁሉ ይመላለሳሉ።