ምዕራፍ 25 (1)

1 እነዚህም ደግሞ የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዱአቸው የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው።

2 የእግዚአብሔር ክብር ነገርን መሰወር ነው፤ የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው።

3 እንደ ሰማይ ከፍታ እንደ ምድርም ጥልቀት የነገሥታት ልብ አይመረመርም።

4 ከብር ዝገትን አስወግድ፥ ፈጽሞም ይጠራል።

5 ከንጉሥ ፊት ኀጥኣንን አርቅ፥ ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች።

6 በንጉሥ ፊት አትመካ፥ በታላልቆችም ስፍራ አትቁም፤

7 ዓይኖችህ ባዩት በመኰንን ፊት ከምትዋረድ። ወደዚህ ከፍ በል ብትባል ይሻልሃልና።

8 ባልንጀራህ ባሳፈረህ ጊዜ ኋላ እንዳትጸጸት ለክርክር ፈጥነህ አትውጣ፤

9 ክርክርህን ከባልንጀራህ ጋር ተከራከር፤ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ፥

10 የሚሰማ እንዳይነቅፍህ፥ አንተንም ከማነወር ዝም እንዳይል።

11 የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው።

12 የምትሰማን ጆሮ የሚዘልፍ ጠቢብ ሰው እንደ ወርቅ ጉትቻ እንደሚያንጸባርቅም ዕንቍ እንዲሁ ነው።

13 በመከር ወራት የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ፥ እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ነው፤ የጌቶቹን ነፍስ ያሳርፋልና።

14 ስለ ስጦታው በሐሰት የሚመካ ሰው ዝናብ እንደማይከተለው ደመና ነፋስም ነው።

15 በትዕግሥት አለቃ ይለዝባል፥ የገራም ምላስ አጥንትን ይሰብራል።

16 አጥብቀህ እንዳትጠግብ እንዳትተፋውም ማር ባገኘህ ጊዜ የሚበቃህን ብላ።

17 እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር።

18 በባልንጀራው በሐሰት የሚመሰክር እንደ መዶሻና እንደ ሰይፍ እንደ ተሳለም ፍላጻ ነው።

19 ወስላታውን ሰው በመከራ ጊዜ መተማመን እንደ ተሰበረ ጥርስና እንደ ሰለለ እግር ነው።

20 ለሚያዝን ልብ ዝማሬ የሚዘምር፥ ለብርድ ቀን መጐናጸፊያውን እንደሚያስወግድ በቍስልም ላይ እንደ መጻጻ እንዲሁ ነው።

21 ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፥ ቢጠማም ውኃ አጠጣው፤

22 ፍም በራሱ ላይ ትሰበስባለህና፥ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይመልስልሃልና።

23 የሰሜን ነፋስ ወጀብ ያመጣል፤ ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቈጣል።

24 ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ በሰገነት ማዕዘን መቀመጥ ይሻላል።

25 የቀዘቀዘ ውኃ ለተጠማች ነፍስ ደስ እንደሚያሰኝ፥ ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ምስራች እንዲሁ ነው።

26 በኀጥእ ፊት የሚወድቅ ጻድቅ እንደደፈረሰ ፈሳሽና እንደ ረከሰ ምንጭ ነው።

27 ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፤ እንዲሁም የራስን ክብር መፈላለግ አያስከብርም።

28 ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፥ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው።