ምዕራፍ 9

1 ጥበብ ቤትዋን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶችዋን አቆመች።

2 ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋን ደባለቀች፥ ማዕድዋን አዘጋጀች።

3 ባሪያዎችዋን ልካ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ጠራች።

4 አላዋቂ የሆነ ወደዚህ ፈቀቅ ይበል፤ አእምሮ የጐደላቸውንም እንዲህ አለች።

5 ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ የደባለቅሁትንም የወይን ጠጅ ጠጡ።

6 አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ።

7 ፌዘኛን የሚገሥጽ ለራሱ ስድብን ይቀበላል፥ ኅጥአንም የሚዘልፍ ነውርን ያገኛል።

8 ፌዘኛን አትገሥጽ እንዳይጠላህ፤ ጠቢብን ገሥጽ ይወድድህማል።

9 ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፥ ጥበብንም ያበዛል፤ ጽድቅንም አስተምረው፥ እውቀትንም ያበዛል።

10 የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው።

11 ዘመንህ በእኔ ይበዛልና፥ የሕይወትህም ዕድሜ ይጨመርልሃልና።

12 ጠቢብ ብትሆን ለራስህ ጠቢብ ትሆናለህ፥ ፌዘኛም ብትሆን ፌዘኛነትህን ለብቻህ ትሸከማለህ።

ፍን [የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።] ልጄ ለራስህ አዋቂ ብትሆን ለባልንጀራህም አዋቂ ትሆናለህ፤ ለራስህ ክፉ ብትሆን ግን ክፋትህን ትማራለህ። ሐሰትን የሚያዘጋጅ ሰው ነፋሳትን እንደሚያዘጋጅ ሰው ነው፤ የሚበርር ወፍንም እንደሚከተል ይመስላል። የወይኑ ቦታ መንገዱን ተወ፤ የሚሠማራባትን መንገድ ዘነጋ፤ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል ለጥም ወደ ተሠራች አገር ይሄዳል፤ የማያፈራ የማይጠቅም ገንዘብንም በእጁ ይሰበስባል።

13 ሰነፍ ሴት ሁከተኛ ናት፤ አሳብ የላትም፥ አንዳችም አታውቅም።

14 በቤትዋ ደጅ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ በወንበር ላይ ትቀመጣለች፥

15 በመንገድ የሚያልፉትን አካሄዳቸውንም ያቀኑትን ለመጥራት።

16 አላዋቂ የሆነ ወደዚህ ፈቀቅ ይበል፤ አእምሮ የጐደለውንም እንዲህ አለች።

17 የስርቆት ውኃ ይጣፍጣል፥ የተሸሸገም እንጀራ ደስ ያሰኛል።

18 ነገር ግን እርሱ ሙታን ከዚያ እንዳሉ፥ እድምተኞችዋም በሲኦል ጥልቀት እንዳሉ አያውቅም።