ምዕራፍ 36።

1፤ ከዮሴፍ ልጆች ወገኖች የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጆች ወገን አለቆች ቀረቡ፥ በሙሴና በእስራኤልም ልጆች አባቶች አለቆች ፊት ተናገሩ፤

2፤ አሉም። ምድሪቱን ለእስራኤል ልጆች ርስት አድርገህ በዕጣ ከፍለህ ትሰጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር አንተን ጌታችንን አዘዘህ፤ እግዚአብሔርም የወንድማችንን የሰለጰዓድን ርስት ለሴቶች ልጆቹ ትሰጥ ዘንድ አንተን ጌታችንን አዘዘ።

3፤ ከሌላም ከእስራኤል ልጆች ነገድ ባል ቢያገቡ፥ ርስታቸው ከአባቶቻችን ርስት ይነቀላል፥ እነርሱም ለሚሆኑበት ለሌላው ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም የርስታችን ዕጣ ይጐድላል።

4፤ ለእስራኤልም ልጆች ኢዮቤልዩ በመጣ ጊዜ ርስታቸው ለሚሆኑበት ነገድ ርስት ይጨመራል፤ እንደዚህም ርስታቸው ከአባቶቻችን ነገድ ርስት ይጐድላል።

5፤ ሙሴም የእስራኤልን ልጆች እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። የዮሴፍ ልጆች ነገድ በእውነት ተናገሩ።

6፤ እግዚአብሔር ስለ ሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ የወደዱትን ያግቡ፤ ነገር ግን ከአባታቸው ነገድ ብቻ ያግቡ።

7፤ እንደዚህም የእስራኤል ልጆች ርስት ከነገድ ወደ ነገድ ምንም አይተላለፍ፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ወደ አባቶቹ ነገድ ርስት ይጠጋ።

8፤ ከእስራኤልም ልጆች እያንዳንዱ ሰው የአባቶቹን ርስት ይወርስ ዘንድ፥ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ ርስት ያላት ሴት ልጅ ሁሉ ከአባትዋ ነገድ ባል ታግባ።

9፤ እንደዚህም ከአንድ ነገድ ወደ ሌላ ነገድ ምንም ርስት አይተላለፍ ከእስራኤልም ልጆች ነገድ እያንዳንዱ ወደ ርስቱ ይጠጋ።

10፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው እንዲሁ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች አደረጉ።

11፤ የሰለጰዓድ ልጆች ማህለህ፥ ቲርጻ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ኑዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ።

12፤ ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ልጆች ወገኖች ባሎቻቸውን አገቡ፥ ርስታቸውም በአባታቸው ነገድ ጸና።

13፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የእስራኤልን ልጆች በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ሜዳ ያዘዛቸው ትእዛዝና ፍርድ እነዚህ ናቸው።