ምዕራፍ 31።

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

2፤ ስለ እስራኤል ልጆች በቀል ምድያማውያንን ተበቀል፤ ከዚያም በኋላ ወደ ወገኖችህ ትከማቻለህ።

3፤ ሙሴም ሕዝቡን። ከእናንተ መካከል ሰዎች ለጦርነት ይሰለፉ፤ ስለ እግዚአብሔር በቀል ምድያምን ይበቀሉ ዘንድ በምድያም ላይ ይሂዱ፤

4፤ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ከየነገዱ አንድ ሺህ ሰው ወደ ጦርነት ስደዱ ብሎ ተናገራቸው።

5፤ ከእስራኤልም አእላፋት አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ፥ ለጦርነት የተሰለፉ ሰዎች ተሰጡ።

6፤ ሙሴም ከየነገዱ አንድ አንድ ሺህ ወደ ጦርነት ሰደደ፤ እነርሱንና የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሐስን ወደ ጦርነት ሰደዳቸው፤ የመቅደሱንም ዕቃ የሚነፋውንም መለከት በእጁ ሰጠው።

7፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ከምድያም ጋር ተዋጉ፥ ወንዶችንም ሁሉ ገደሉ።

8፤ ከተገደሉትም ጋር የምድያምን ነገሥታት ገደሉአቸው፤ አምስቱም የምድያም ነገሥታት ኤዊ፥ ሮቆም፥ ሱር፥ ሑር፥ ሪባ ነበሩ፤ የቢዖርንም ልጅ በለዓምን ደግሞ በሰይፍ ገደሉት።

9፤ የእስራኤልም ልጆች የምድያምን ሴቶችና ልጆቻቸውን ማረኩ፤ እንስሶቻቸውንና መንጎቻቸውንም ዕቃቸውንም ሁሉ በዘበዙ።

10፤ የተቀመጡባቸውን ከተሞቻቸውን ሁሉ ሰፈሮቻቸውንም ሁሉ በእሳት አቃጠሉ።

11፤ የሰውንና የእንስሳን ምርኮና ብዝበዛ ሁሉ ወሰዱ።

12፤ የማረኩአቸውንም ሰዎች ምርኮውንና ብዝበዛውን ወደ ሙሴና ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር፥ በዮርዳኖስም አጠገብ በኢያሪኮ ፊት ለፊት በሞዓብ ሜዳ ወዳለው ሰፈር አመጡ።

13፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም የማኅበሩም አለቆች ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ ሊገናኙአቸው ወጡ።

14፤ ሙሴም ከዘመቻ በተመለሱት በጭፍራ አለቆች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ።

15፤ ሙሴም አላቸው። በውኑ ሴቶችን ሁሉ አዳናችኋቸውን?

16፤ እነሆ፥ እነዚህ በፌጎር ምክንያት በበለዓም ምክር እግዚአብሔርን ይበድሉ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ዕንቅፋት ሆኑ፤ ስለዚህም በእግዚአብሔር ማኅበር ላይ መቅሠፍት ሆነ።

17፤ አሁን እንግዲህ ከልጆቹ ወንዱን ሁሉ ግደሉ፥ ወንድንም በመኝታ የሚያውቁትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ።

18፤ ወንድን የማያውቁትን ሴቶች ልጆችን ሁሉ ግን ለራሳችሁ አድኑአቸው።

19፤ ከሰፈሩም ውጭ ሰባት ቀን ስፈሩ፤ ሰውን የገደለ ሁሉ የተገደለውንም የዳሰሰ ሁሉ፥ እናንተ የማረካችኋቸውም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ።

20፤ ልብስንም፥ ከቁርበትም የተዘጋጀውን ሁሉ፥ ከፍየልም ጠጕር ከእንጨትም የተሠራውን ሁሉ ንጹሕ አድርጉ።

21፤ ካህኑም አልዓዛር ከሰልፍ የመጡትን ሰዎች አላቸው። እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘው የሕጉ ሥርዓት ይህ ነው፤

22፤ ወርቁንና ብሩን፥ ናሱንም፥ ብረቱንም፥ ቆርቆሮውንም፥

23፤ አረሩንም፥ በእሳት ለማለፍ የሚችለውን ሁሉ በእሳት ታሳልፉታላችሁ፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በማንጻት ውኃ ደግሞ ይጠራል። በእሳትም ለማለፍ የማይችለውን በውኃ ታሳልፉታላችሁ።

24፤ በሰባተኛውም ቀን ልብሳችሁን እጠቡ፥ ንጹሕም ትሆናላችሁ፤ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ትቀርባላችሁ።

25፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

26፤ አንተና ካህኑ አልዓዛር የማኅበሩም አባቶች አለቆች የተማረኩትን ሰውና እንስሳ ቍጠሩ።

27፤ ምርኮውንም በተዋጉትና ወደ ሰፍል በወጡት፥ በማኅበሩም ሁሉ መካከል አስተካክለህ ክፈል።

28፤ ከእነዚያም ከተዋጉት ወደ ሰልፍም ከወጡት ሰልፈኞች ዘንድ፥ ከሰዎችም ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከአምስት መቶ አንድ ለእግዚአብሔር ግብር አውጣ።

29፤ ከድርሻቸው ወስደህ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ለካህኑ ለአልዓዛር ስጠው።

30፤ ከእስራኤልም ልጆች ድርሻ ከሰዎች ከበሬዎችም ከአህዮችም ከመንጎችም ከከብቶችም ሁሉ ከአምሳ አንድ ትወስዳለህ፥ የእግዚአብሔርንም ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ለሌዋውያን ትሰጣለህ።

31፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።

32፤ ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎችም ከወሰዱት ብዝበዛ ያስቀሩት ምርኮ እንዲህ ሆነ፤ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥

33፤34፤ ሰባ ሁለት ሺህ በሬዎች፥ ስድሳ አንድ ሺህ አህዮች፥

35፤ ወንድ ከማያውቁ ሴቶችም ሠላሳ ሁለት ሺህ ነፍስ።

36፤ በዘመቻም ለነበሩ ሰዎች ድርሻ የሆነ እኵሌታ ከበግ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበረ፥

37፤ ከበጎችም የእግዚአብሔር ግብር ስድስት መቶ ሰባ አምስት ነበረ።

38፤ በሬዎችም ሠላሳ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሰባ ሁለት ነበረ።

39፤ አህዮቹም ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ስድሳ አንድ ነበረ።

40፤ ሰዎቹም አሥራ ስድስት ሺህ ነበሩ፤ የእግዚአብሔርም ግብር ሠላሳ ሁለት ነበረ።

41፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን የሆነውን ግብር ለካህኑ ለአልዓዛር ሰጠው።

42፤ ከእስራኤል ልጆች እኩሌታም፥ ወደ ሰልፍ ከወጡት ወንዶች ላይ ሙሴ የለየው፥

43፤ የማኅበሩ ድርሻ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥

44፤ ሠላሳ ስድስት ሺህ በሬዎች፥

45፤ ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮች፥

46፤ አሥራ ስድስት ሺህ ሰዎች ነበሩ።

47፤ ከእስራኤል ልጆች ድርሻ ሙሴ ከሰውና ከእንስሳ ከአምሳ አንድ ወሰደ፥ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ማደሪያ አገልግሎት ለሚጠብቁ ሌዋውያን ሰጠ።

48፤ በሠራዊት አእላፋት ላይ የተሾሙት አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች፥ ወደ ሙሴ ቀረቡ፥

49፤ ሙሴንም። እኛ ባሪያዎችህ ወደ ሰልፍ የወጡትን ከእጃችን በታች ያሉትን ቈጠርን፥ ከእኛም አንድ አልጐደለም።

50፤ ሰውም ሁሉ ካገኘው ከወርቅ ዕቃ፥ ከእግር አልቦም፥ ከአምባርም፥ ከቀለበትም፥ ከጕትቻም፥ ከድሪውም ለነፍሳችን በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይልን ዘንድ ለእግዚአብሔር መባ አምጥተናል አሉት።

51፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁንና በልዩ ልዩ የተሠራውን ዕቃ ሁሉ ከእጃቸው ተቀበሉ።

52፤ ሻለቆችም የመቶ አለቆችም ለእግዚአብሔር ለማንሣት ቍርባን ያቀረቡት ወርቅ ሁሉ አሥራ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ አምሳ ሰቅል ነበረ።

53፤ ወደ ሰልፍ የወጡ ሰዎች ሁሉ ከምርኮአቸው ለራሳቸው ወሰዱ።

54፤ ሙሴና ካህኑ አልዓዛርም ወርቁን ከሻለቆችና ከመቶ አለቆች ወስደው በእግዚአብሔር ፊት ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ወደ መገናኛው ድንኳን አገቡት።