ምዕራፍ 28።

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

2፤ የእስራኤልን ልጆች እንዲህ ብለህ እዘዛቸው። መብሌን፥ ለእኔ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የተደረገውን ቍርባኔን፥ መባዬን በየጊዜው ታቀርቡልኝ ዘንድ ጠብቁ።

3፤ እንዲህም በላቸው። በእሳት ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት ቍርባን ይህ ነው፤ ለዘወትር ለሚቃጠል መሥዋዕት ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች ዕለት ዕለት ታቀርባላችሁ።

4፤ አንዱን ጠቦት በማለዳ፥ ሌላውንም ጠቦት በማታ አቅርብ፤

5፤ ለእህልም ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት ታቀርባለህ።

6፤ በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የቀረበ በሲና ተራራ የተሠራ ለዘወትር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

7፤ የመጠጡ ቍርባን ለአንድ ጠቦት የኢን መስፈሪያ አራተኛው እጅ ነው፤ በመቅደሱ ውስጥ ለእግዚአብሔር ለመጠጥ ቍርባን መጠጥ ታፈስሳለህ።

8፤ ሌላውንም ጠቦት በማታ ጊዜ ታቀርባለህ፤ የእህሉን ቍርባንና የመጠጡን ቍርባን በማለዳ እንዳቀረብህ በእሳት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን ታቀርበዋለህ።

9፤ በሰንበትም ቀን ነውር የሌለባቸውን ሁለት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥ ለእህልም ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥ የመጠጡንም ቍርባን ታቀርባላችሁ።

10፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕት ሌላ፥ ከመጠጡም ቍርባን ሌላ፥ በየሰንበቱ ሁሉ የምታቀርቡት የሚቃጠለው መሥዋዕት ይህ ነው።

11፤ በወሩም መባቻ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈን፥ አንድ አውራ በግ፥ ነውርም የሌለባቸውን ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥

12፤ ለእያንዳንዱም ወይፈን ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት፥ ለአውራው በግም ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ መልካም ዱቄት፥

13፤ ለእያንዳንዱም ጠቦት ለእህል ቍርባን በዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት ታቀርባላችሁ።

14፤ የመጠጥ ቍርባናቸውም ለአንድ ወይፈን የኢን ግማሽ፥ ለአውራው በግም የኢን ሢሶ፥ ለአንዱም ጠቦት የኢን አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ይሆናል፤ ይህ ለዓመቱ የወር መባቻ ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።

15፤ ለእግዚአብሔርም ለኃጢአት መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቍርባን ሌላ ይቀርባል።

16፤ በመጀመሪያው ወር ከወሩም በአሥራ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።

17፤ ከዚህም ወር በአሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ይሆናል ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላላችሁ።

18፤ በመጀመሪያው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆናል፤ በእርሱም የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።

19፤ በእሳትም የተደረገውን ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፤ ነውር የሌለባቸው ይሁኑላችሁ።

20፤ የእህል ቍርባናቸውንም በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለአንድ ወይፈን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአውራውም በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥

21፤ ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ።

22፤ ማስተስረያ የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።

23፤ ማልዶ ከሚቀርበው በዘወትር ከሚቃጠል መሥዋዕት ሌላ እነዚህን ታቀርባላችሁ።

24፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚደረገውን የቍርባኑን መብል ሰባት ቀን በየዕለቱ እንዲሁ ታቀርባላችሁ፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከመጠጡ ቍርባን ሌላ ይቀርባል።

25፤ በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።

26፤ ደግሞ በበኵራት ቀን ከሰባቱ ሱባዔ በዓላችሁ አዲሱን የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ባቀረባችሁ ጊዜ፥ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል፤ የተግባርን ሥራ ሁሉ አትሥሩበት።

27፤ ለእግዚአብሔርም ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠለውን መሥዋዕት ታቀርባላችሁ፤ ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ ሰባት የአንድ ዓመት ተባት የበግ ጠቦቶች፥

28፤ ለእህል ቍርባናቸው በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄት፥ ለእያንዳንዱ ወይፈን ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሦስት እጅ፥ ለአንዱም አውራ በግ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ፥

29፤ ለሰባቱም ጠቦቶች ለእያንዳንዱ ጠቦት ከመስፈሪያው አሥረኛ እጅ ታቀርባላችሁ።

30፤ ማስተስረያ የሚሆንላችሁን አንድ አውራ ፍየል ለኃጢአት መሥዋዕት ታቀርባላችሁ።

31፤ በዘወትር ከሚቃጠለው መሥዋዕትና ከእህሉ ቍርባን ሌላ እነርሱንና የመጠጥ ቍርባናቸውን ታቀርባላችሁ፤ ነውርም የሌለባቸው ይሁኑ።