ምዕራፍ 27።

1፤ ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ወገኖች፥ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጅ የገለዓድ ልጅ የኦፌር ልጅ የሰለጰዓድ ሴቶች ልጆች ቀረቡ፤ የእነዚህም ሴቶች ልጆች ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ።

2፤ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ አጠገብ በሙሴና በካህኑ በአልዓዛር በአለቆቹም በማኅበሩም ሁሉ ፊት ቆመው።

3፤ አባታችን በምድረ በዳ ሞተ፤ በራሱ ኃጢአት ሞተ እንጂ ከቆሬ ጋር በእግዚአብሔር ላይ በተሰበሰቡ ወገን መካከል አልነበረም፤ ወንዶችም ልጆች አልነበሩትም።

4፤ ወንድ ልጅስ ባይኖረው የአባታችን ስም ከወገኑ መካከል ለምን ይጠፋል? በአባታችን ወንድሞች መካከል ርስትን ስጠን አሉ።

5፤ ሙሴም ነገራቸውን በእግዚአብሔር ፊት አቀረበ።

6፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

7፤ የሰለጰዓድ ልጆች እውነት ተናግረዋል፤ በአባታቸው ወንድሞች መካከል የርስት ድርሻ ስጣቸው፤ የአባታቸውን ርስት ለእነርሱ አሳልፈህ ስጥ።

8፤ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ሰው ቢሞት ወንድ ልጅም ባይኖረው፥ ርስቱ ለሴት ልጁ ይለፍ፤

9፤ ሴት ልጅም ባትኖረው ርስቱን ለወንድሞቹ ስጡ፤

10፤ ወንድሞችም ባይኖሩት ርስቱን ለአባቱ ወንድሞች ስጡ፤

11፤ የአባቱም ወንድሞች ባይኖሩት ከወገኑ ለቀረበ ዘመድ ርስቱን ስጡ እርሱም ይውረሰው፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘ ለእስራኤል ልጆች ሥርዓትና ፍርድ ይሁን።

12፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ወደዚህ ወደ ዓባሪም ተራራ ውጣ፥ ለእስራኤልም ልጆች የሰጠኋትን ምድር እይ፤

13፤ ባየሃትም ጊዜ ወንድምህ አሮን እንደ ተከማቸ አንተ ደግሞ ወደ ወገንህ ትከማቻለህ።

14፤ እናንተ በጺን ምድረ በዳ በማኅበሩ ጠብ በቃሌ ላይ ዐምፃችኋልና፥ በእነርሱም ፊት በውኃው ዘንድ አልቀደሳችሁኝምና። ይህም በጺን ምድረ በዳ በቃዴስ ያለው የመሪባ ውኃ ነው።

15፤ ሙሴም እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

16፤17፤ የእግዚአብሔር ማኅበር እረኛ እንደሌለው መንጋ እንዳይሆን፥ በፊታቸው የሚወጣውን በፊታቸውም የሚገባውን የሚያስወጣቸውንም የሚያስገባቸውንም ሰው የሥጋ ሁሉ መንፈስ አምላክ እግዚአብሔር በማኅበሩ ላይ ይሹመው።

18፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። መንፈስ ያለበትን ሰው የነዌን ልጅ ኢያሱን ወስደህ እጅህን በላዩ ጫንበት፤

19፤ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቁመው፥ እነርሱም እያዩ እዘዘው።

20፤ የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲታዘዙት ከክብርህ አኑርበት።

21፤ በካህኑም በአልዓዛር ፊት ይቁም፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት በኡሪም ፍርድ ይጠይቅለት፤ እርሱ ከእርሱም ጋር የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በቃሉ ይውጡ፥ በቃሉም ይግቡ።

22፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ኢያሱንም ወስዶ በካህኑ በአልዓዛርና በማኅበሩ ሁሉ ፊት አቆመው፤

23፤ እግዚአብሔርም በሙሴ እንደ ተናገረ፥ እጁን በላዩ ጫነበት፥ አዘዘውም።