ምዕራፍ 9።

1፤ በዚህም ወር በሀያ አራተኛው ቀን የእስራኤል ልጆች ጾመው፥ ማቅም ለብሰው፥ በላያቸውም ትቢያ ነስንሰው ተከማቹ።

2፤ የእስራኤልም ዘር ከእንግዶች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ፥ ቆመውም ኃጢአታቸውንና የአባቶቻቸውን ኃጢአት ተናዘዙ።

3፤ በየስፍራቸውም ቆመው የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን የሕግ መጽሐፍ የቀን ሩብ ያህል አነበቡ፤ ሦስት የቀን ሩብም ያህል ተናዘዙ፥ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ሰገዱ።

4፤ ሌዋውያኑም ኢያሱና ባኒ፥ ቀድምኤል፥ ሰበንያ፥ ቡኒ፥ ሰራብያ፥ ባኒ፥ ክናኒ በደረጃዎች ላይ ቆመው ወደ አምላካቸው ወደ እግዚአብሔር በታላቅ ድምፅ ጮኹ።

5፤ ሌዋውያኑም ኢያሱ፥ ቀድምኤል፥ ባኒ፥ አሰበንያ፥ ሰራብያ፥ ሆዲያ፥ ሰበንያ፥ ፈታያ እንዲህ አሉ። ቆማችሁ ከዘላለም እስከ ዘላለም አምላካችንን እግዚአብሔርን ባርኩ። እንዲህም በሉ። በበረከትና በምስጋና ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለው ክቡር ስምህ ይባረክ።

6፤ አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፤ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፤ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ።

7፤ አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ፤ አብራምን መረጥህ፥ ከዑር ከላውዴዎንም አወጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም አልኸው፤

8፤ ልቡም በፊትህ የታመነ ሆኖ አገኘኸው፤ የከነዓናዊውንና የኬጢያዊውን የአሞራዊውንም የፌርዛዊውንም የኢያቡሳዊውንም የጌርጌሳዊውንም ምድር ለእርሱና ለዘሩ ትሰጥ ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ።

9፤ በግብጽም ሳሉ የአባታችንን መከራ አየህ፥ በኤርትራ ባሕርም ሳሉ ጩኸታቸውን ሰማህ፤

10፤ እንደ ታበዩባቸውም አውቀህ ነበርና በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትና ተአምራት አሳየህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው ስምህን አስጠራህ።

11፤ ከፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፥ በባሕሩም መካከል በደረቅ አልፉ፤ ጠላቶቻቸውን ግን ድንጋይ ለጥልቅ ውኃ እንዲጣል በቀላይ ውስጥ ጣልሃቸው።

12፤ የሚሄዱበትንም መንገድ ታበራላቸው ዘንድ በቀን በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ መራሃቸው።

13፤ ወደ ሲናም ተራራ ወረድህ፥ ከሰማይም ተናገርሃቸው፤ ቅኑን ፍርድና እውነቱን ሕግ መልካሙንም ሥርዓትና ትእዛዝ ሰጠሃቸው፤

14፤ የተቀደሰውንም ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፥ ትእዛዝንና ሥርዓትን ሕግንም በባሪያህ በሙሴ እጅ አዘዝሃቸው።

15፤ ለራባቸውም ከሰማይ እንጀራ ሰጠሃቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አመጣህላቸው፤ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው ይወርሱ ዘንድ አዘዝሃቸው።

16፤ ነገር ግን እነርሱና አባቶቻችን ታበዩ፥ አንገታቸውንም አደንደኑ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥

17፤ ለመስማትም እንቢ አሉ፥ ያደረግህላቸውንም ተአምራት አላሰቡም፤ አንገታቸውንም አደንደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ይመለሱ ዘንድ አለቃ አደረጉ፤ አንተ ግን ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ፥ ለቍጣም የምትዘገይ፥ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ፥ አልተውሃቸውም።

18፤ ቀልጦ የተሠራውንም እምቦሳ አድርገው። ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው ባሉ ጊዜ፥ እጅግም ባስቈጡህ ጊዜ፥

19፤ አንተ በምሕረትህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፤ በመንገድም ይመራቸው ዘንድ የደመና ዓምድ በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ ያበራላቸው ዘንድ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልራቀም።

20፤ ያስተምራቸውም ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፥ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፥ ለጥማታቸውም ውኃ ሰጠሃቸው።

21፤ አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብሃቸው፥ ምንም አላጡም፤ ልብሳቸውም አላረጅም፥ እግራቸውም አላበጠም።

22፤ መንግሥታትንና አሕዛብን ከፍለህ ሰጠሃቸው፤ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ።

23፤ ልጆቻቸውንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፤ ይገቡና ይወርሱ ዘንድ ለአባቶቻቸው ወደ ተናገርህላቸውም ምድር አገባሃቸው።

24፤ ልጆቹም ገብተው ምድሩን ወረሱ፥ የምድሩን ሰዎች ከነዓናውያንን በፊታቸው አዋረድህ፤ የሚወድዱትንም ነገር ያደረጉባቸው ዘንድ እነርሱንና ነገሥታቶቻቸውን የምድሩንም አሕዛብ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው።

25፤ ምሽጎቹንም ከተሞች የሰባውንም ምድር ወሰዱ፤ መልካሙን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጕድጓዶች፥ ወይኖቹንና ወይራዎቹን ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፤ በሉም፥ ጠገቡም፥ ወፈሩም፥ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው።

26፤ ነገር ግን እንቢተኞች ነበሩ፥ ዐመፁብህም፥ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፤ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፥ እጅግም አስቈጡህ።

27፤ ስለዚህ ለጠላቶቻቸው እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፥ አስጨነቁአቸውም፤ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፥ ከሰማይም ሰማሃቸው፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳኑአቸውን ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው።

28፤ ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፤ በጠላቶቻቸው እጅ ተውሃቸው፥ ገዙአቸውም፤ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፤

29፤ ወደ ሕግህም ትመልሳቸው ዘንድ አስመሰከርህባቸው፤ ነገር ግን ታበዩ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ሰውም ባደረገው ጊዜ በሕይወት የሚኖርበትን ፍርድህን ተላለፉ፤ ትከሻቸውንም ሰጡ፥ አንገታቸውን አደነደኑ፥ አልሰሙምም።

30፤ ነገር ግን ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው፥ በነቢያትህም እጅ በመንፈስህ መሰከርህባቸው፤ አላደመጡም፥ ስለዚህም በምድር አሕዛብ እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው።

31፤ ነገር ግን አንተ ቸርና መሐሪ አምላክ ነህና በምሕረትህ ብዛት ፈጽመህ አላጠፋሃቸውም፥ አልተውሃቸውምም።

32፤ አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነቢያቶቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ።

33፤ በደረሰብንም ነገር ሁሉ አንተ ጻድቅ ነህ፥ አንተ እውነት አድርገሃልና፥ እኛም ኃጢአት አድርገናል።

34፤ ነገሥታቶቻችንም አለቆቻችንም ካህናቶቻችንም አባቶቻችንም ሕግህን አልጠበቁም፥ የመሰከርህባቸውንም ትእዛዝህንና ምስክርህን አልሰሙህም።

35፤ በመንግሥታቸውም በሰጠሃቸውም ታላቅ በጎነትህ፥ በፊታቸውም በሰጠኸው በሰባው ምድር አላመለኩህም፥ ከክፉም ሥራቸው አልተመለሱም።

36፤ እነሆ፥ ዛሬ ባሪያዎች ነን፤ ፍሬዋንና በረከትዋን ይበሉ ዘንድ ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር፥ እነሆ፥ በእርስዋ ባሪያዎች ነን፥

37፤ ስለ ኃጢአታችንም ለሾምህብን ነገሥታት በረከትዋን ታበዛለች፤ ሰውነታችንንም ይገዛሉ፥ በእንስሶቻችንም የሚወድዱትን ያደርጋሉ፥ እኛም በጽኑ መከራ ላይ ነን።

38፤ ስለዚህም ሁሉ የታመነውን ቃል ኪዳን አድርገን እንጽፋለን፤ አለቆቻችንም ሌዋውያኖቻችንም ካህናቶቻችንም ያትሙበታል።