ምዕራፍ 7።

1፤ የዛፍ ፍሬና የወይን ፍሬ ከተለቀሙ በኋላ እንደ ቀረው ቃርሚያ ሆኛለሁና ወዮልኝ! መብል የሚሆን ዘለላ፥ ነፍሴም የተመኘችው በመጀመሪያ የበሰለው በለስ የለም።

2፤ ደግ ሰው ከምድር ጠፍቶአል፥ በሰውም መካከል ቅን የለም፤ ሁሉ ደምን ለማፍሰስ ያደባሉ፥ ሰውም ሁሉ ወንድሙን በመረብ ለመያዝ ይከታተለዋል።

3፤ እጆቻቸውን ለክፋት ያነሣሉ፤ አለቃውና ፈራጁ ጉቦን ይፈልጋሉ፥ ትልቁም ሰው እንደ ነፍሱ ምኞት ይናገራል፤ እንዲሁም ክፋትን ይጐነጕናሉ።

4፤ ከእነርሱም ሁሉ የተሻለው እርሱ እንደ አሜከላ ነው፥ ከሁሉም ቅን የሆነው እንደ ኵርንችት ነው፤ ጠባቆችህ የሚጐበኙበት ቀን መጥቶአል፤ አሁን ይሸበራሉ።

5፤ ባልንጀራን አትመኑ፥ በወዳጅም አትታመኑ፤ የአፍህን ደጅ በብብትህ ከምትተኛው ጠብቅ።

6፤ ወንድ ልጅ አባቱን ይንቃልና፥ ሴት ልጅ በእናትዋ ላይ፥ ምራቲቱም በአማትዋ ላይ ትነሣለችና፥ የሰው ጠላቶች የቤቱ ሰዎች ናቸውና።

7፤ እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፥ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አምላኬም ይሰማኛል።

8፤ ጠላቴ ሆይ፥ ብወድቅ እነሣለሁና፥ በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና በእኔ ላይ ደስ አይበልሽ።

9፤ በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁና እስኪምዋገትልኝ ድረስ፥ ፍርድን ለእኔ እስኪያደርግ ድረስ ቍጣውን እታገሣለሁ። ወደ ብርሃን ያወጣኛል፥ ጽድቅንም አያለሁ።

10፤ ጠላቴም ታያለች፥ እኔንም። አምላክህ እግዚአብሔር ወዴት ነው? ያለች በእፍረት ትከደናለች።

11፤ ዓይኖቼ ይመለከቱአታል፤ አሁን እንደ መንገድ ጭቃ ትረገጣለች። ቅጥርሽ በሚሠራበት በዚያ ቀን ድንበርሽ ትስፋፋለች።

12፤ በዚያ ቀን ከአሦርና ከግብጽ ከተሞች፥ ከግብጽ እስከ ወንዙ፥ ከባሕርም እስከ ባሕር፥ ከተራራም እስከ ተራራ ድረስ ወደ አንቺ ይመጣሉ።

13፤ ምድሪቱ ግን በሚኖሩባት በሥራቸው ፍሬ ምክንያት ባድማ ትሆናለች።

14፤ በቀርሜሎስ መካከል ባለው ዱር ብቻቸውን የተቀመጡት ሰዎችህ፥ የርስትህን በጎች፥ በበትርህ አግድ፤ እንደ ቀደመውም ዘመን በበሳንና በገለዓድ ይሰማሩ።

15፤ ከግብጽ ምድር እንደ ወጣህበት ዘመን ተአምራትን አሳያቸዋለሁ።

16፤ አሕዛብ አይተው በጕልበታቸው ሁሉ ያፍራሉ፤ እጃቸውን በአፋቸው ላይ ያኖራሉ፥ ጆሮአቸውም ትደነቍራለች፤

17፤ እንደ እባብም መሬት ይልሳሉ፥ እንደ ምድርም ተንቀሳቃሾች እየተንቀጠቀጡ ከግንባቸው ይመጣሉ፤ ፈርተውም ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ይመጣሉ፥ ስለ አንተም ይፈራሉ።

18፤ በደልን ይቅር የሚል፥ የርስቱንም ቅሬታ ዓመፅ የሚያሳልፍ እንደ አንተ ያለ አምላክ ማን ነው? ምሕረትን ይወድዳልና ቍጣውን ለዘላለም አይጠብቅም።

19፤ ተመልሶ ይምረናል፤ ክፋታችንንም ይጠቀጥቃል፥ ኃጢአታችንንም በባሕሩ ጥልቅ ይጥለዋል።

20፤ ከቀድሞ ዘመን ጀምረህ ለአባቶቻችን የማልህላቸውን እውነት ለያዕቆብ፥ ምሕረትንም ለአብርሃም ታደርጋለህ።