ምዕራፍ 27

1 ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤

2 አስረውም ወሰዱት፥ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት።

3 በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ።

4 ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን። እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ።

5 ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ።

6 የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው። የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ።

7 ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት።

8 ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ።

9 በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው። ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥

10 ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ።

11 ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም። አንተ አልህ አለው።

12 የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም።

13 በዚያን ጊዜ ጲላጦስ። ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው።

14 ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም።

15 በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው።

16 በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው።

17 እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ። በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤

18 በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።

19 እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ። ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት።

20 የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ።

21 ገዢውም መልሶ። ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም። በርባንን አሉ።

22 ጲላጦስ። ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም። ይሰቀል አሉ።

23 ገዢውም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን። ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ።

24 ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ።

25 ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ።

26 በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ።

27 በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ አከማቹ።

28 ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት፥

29 ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤

30 ተፉበትም መቃውንም ይዘው ራሱን መቱት።

31 ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትም ወሰዱት።

32 ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት።

33 ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥

34 በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም።

35 ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥

36 በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር።

37 ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ።

38 በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዶች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ።

39 የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና።

40 ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ አሉት።

41 እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ።

42 ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን።

43 በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው።

44 ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር።

45 ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።

46 በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው።

47 በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ።

48 ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው።

49 ሌሎቹ ግን። ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ።

50 ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ።

51 እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤

52 መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤

53 ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ።

54 የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው። ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ።

55 ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤

56 ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።

57 በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤

58 ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው።

59 ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥

60 ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ።

61 መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ።

62 በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና።

63 ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን።

64 እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት።

65 ጲላጦስም። ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው።

66 እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ።