ምዕራፍ 4።

1፤ እነሆ፥ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞችና ኃጢአትን የሚሠሩ ሁሉ ገለባ ይሆናሉ፤ የሚመጣውም ቀን ያቃጥላቸዋል፥ ሥርንና ቅርንጫፍንም አይተውላቸውም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

2፤ ነገር ግን ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች፥ ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል፤ እናንተም ትወጣላችሁ፥ እንደ ሰባም እምቦሳ ትፈነጫላችሁ።

3፤ በምሠራበት ቀን በደለኞች ከእግራችሁ ጫማ በታች አመድ ይሆናሉና እናንተ ትረግጡአቸዋላችሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

4፤ ለእስራኤል ሁሉ ሥርዓትንና ፍርድን አድርጌ በኮሬብ ያዘዝሁትን የባሪያዬን የሙሴን ሕግ አስቡ።

5፤ እነሆ፥ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ነቢዩን ኤልያስን እልክላችኋለሁ።

6፤ መጥቼም ምድርን በእርግማን እንዳልመታ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።