ምዕራፍ 21።

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። ለካህናቱ ለአሮን ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው አለው። ማንም ሰው ከሕዝቡ ስለ ሞተው፥

2፤ ከሚቀርበው ዘመዱ፥ ከእናቱ፥ ወይም ከአባቱ፥ ወይም ከወንድ ልጁ፥ ወይም ከሴት ልጁ፥ ወይም ከወንድሙ በቀር አይርከስ።

3፤ ወይም የቀረበችው ያልተጋባች ድንግል እኅቱ በእርስዋ ይርከስ።

4፤ የሕዝቡ አለቃ ራሱን ያጐሰቍል ዘንድ አይርከስ።

5፤ ራሳቸውን አይላጩ፥ ጢማቸውንም አይላጩ፥ ሥጋቸውንም አይንጩ።

6፤ ለአምላካቸው ቅዱሳን ይሁኑ፥ የአምላካቸውንም ስም አያጐስቍሉ፤ የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባንና የአምላካቸውን እንጀራ ያቀርባሉና ቅዱሳን ይሁኑ።

7፤ ለአምላኩ የተቀደሰ ነውና ጋለሞታን ሴት ወይም የረከሰችውን አያግባ፤ ወይም ከባልዋ የተፈታችውን አያግባ።

8፤ የአምላክህን እንጀራ ያቀርባልና ስለዚህ ትቀድሰዋለህ፤ እኔም የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና እርሱ ቅዱስ ይሁንልህ።

9፤ የካህንም ልጅ ራስዋን በግልሙትና ብታረክስ አባትዋን ታረክሰዋለች፤ በእሳት ትቃጠል።

10፤ በራሱም ላይ የቅባት ዘይት የፈሰሰበት፥ የክህነትም ልብስ ይለብስ ዘንድ የተቀደሰ ከወንድሞቹ የበለጠው ካህን ራሱን አይግለጥ ልብሱንም አይቅደድ።

11፤ ወደ በድንም ሁሉ አይግባ፥ በአባቱም ወይም በእናቱ አይርከስ።

12፤ የአምላኩም ቅባት ዘይት ቅዱስነት በላዩ ነውና ከመቅደስ አይውጣ፥ የአምላኩንም መቅደስ አያርክስ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

13፤ እርሱም ሚስትን በድንግልናዋ ያግባ።

14፤ ባልዋ የሞተባትን፥ ወይም የተፋታችውን፥ ወይም ጋለሞታይቱን አያግባ፤ ነገር ግን ከሕዝቡ ድንግሊቱን ያግባ።

15፤ እኔም የምቀድሰው እግዚአብሔር ነኝና በሕዝቡ መካከል ዘሩን አያጐስቍል።

16፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

17፤ ለአሮን እንዲህ ብለህ ንገረው። ከዘርህ በትውልዳቸው ነውር ያለበት ሰው ሁሉ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ።

18፤ ዕውር፥ ወይም አንካሳ፥ ወይም አፍንጫ ደፍጣጣ፥ ወይም፤ ትርፍ አካል ያለው፥

19፤ ወይም እግረ ሰባራ፥ ወይም እጀ ሰባራ፥

20፤ ወይም ጐባጣ፥ ወይም ድንክ፥ ወይም ዓይነ መጭማጫ፥ ወይም እከካም፥ ወይም ቋቍቻም፥ ወይም ጃንደረባ፥ ነውረኛ ሁሉ አይቅረብ።

21፤ ከካህኑ ከአሮን ዘር ነውር ያለበት ሰው የእግዚአብሔርን የእሳት ቍርባን ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ፤ ነውረኛ ነው፤ የአምላኩን እንጀራ ያቀርብ ዘንድ አይቅረብ።

22፤ የቅዱሱንና የቅዱስ ቅዱሳኑን የአምላኩን እንጀራ ይብላ፤

23፤ ነገር ግን ነውረኛ ነውና መቅደሶቼን እንዳያረክስ ወደ መጋረጃው አይግባ፥ ወደ መሠዊያውም አይቅረብ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

24፤ ሙሴም ይህን ለአሮን፥ ለልጆቹም፥ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ ነገረ።