ምዕራፍ 5።

1፤ አቤቱ፥ የሆነብንን አስብ፤ ተመልከት ስድባችንንም እይ።

2፤ ርስታችን ለእንግዶች፥ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ።

3፤ ድሀ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆነዋል።

4፤ ውኃችንን በብር ጠጣን እንጨታችንን በዋጋ ገዛን።

5፤ አሳዳጆቻችን በአንገታችን ላይ ናቸው፤ እኛ ደክመናል ዕረፍትም የለንም።

6፤ ለግብጻውያንና ለአሦራውያን እንጀራ እንጠግብ ዘንድ እጅ ሰጠን።

7፤ አባቶቻችን ኃጢአትን ሠሩ ዛሬም የሉም፤ እኛም በደላቸውን ተሸከምን።

8፤ ባሪያዎች ሠልጥነውብናል፤ ከእጃቸው የሚታደገን የለም።

9፤ ከምድረ በዳ ሰይፍ የተነሣ በሕይወታችን እንጀራችንን እናመጣለን።

10፤ ከሚያቃጥል ከራብ ትኩሳት የተነሣ ቁርበታችን እንደ ምድጃ ጠቈረ።

11፤ በጽዮን ሴቶችን፥ በይሁዳም ከተሞች ደናግልን አጐሰቈሉ።

12፤ አለቆች በእጃቸው ተሰቀሉ፤ የሽማግሌዎች ፊት አልታፈረም።

13፤ ጕልማሶች ወፍጮን ተሸከሙ፥ ልጆችም ከእንጨት በታች ተሰናከሉ።

14፤ ሽማግሌዎች ከአደባባይ፥ ጕልማሶች ከበገናቸው ተሻሩ።

15፤ የልባችን ደስታ ቀርቶአል፤ ዘፈናችን ወደ ልቅሶ ተለውጦአል።

16፤ አክሊል ከራሳችን ወድቆአል፤ ኃጢአት ሠርተናልና ወዮልን!

17፤ ስለዚህ ልባችን ታምሞአል፤ ስለዚህም ነገር ዓይናችን ፈዝዞአል፤

18፤ ስለ ጽዮን ተራራ፥ ባድማ ሆናለችና፥ ቀበሮችም ተመላልሰውባታልና።

19፤ አቤቱ፥ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፤ ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው።

20፤ ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ? ስለ ምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ?

21፤ አቤቱ፥ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፤ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ።

22፤ ነገር ግን ፈጽመህ ጥለኸናል፤ እጅግ ተቈጥተኸናል።