ምዕራፍ 18።

1፤ የእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ በሴሎ ተሰበሰቡ፥ በዚያም የመገናኛውን ድንኳን ተከሉ፤ ምድሩም ጸጥ ብሎ ተገዛላቸው።

2፤ ከእስራኤልም ልጆች ርስት ያልተካፈሉ ሰባት ነገድ ቀርተው ነበር።

3፤ ኢያሱም የእስራኤልን ልጆች አላቸው። የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ምድር ትወርሱ ዘንድ እስከ መቼ ለመግባት ቸል ትላላችሁ?

4፤ ከየነገዱ ሁሉ ሦስት ሦስት ሰዎች ምረጡ፥ እኔም እልካቸዋለሁ፤ ተነሥተውም አገሩን ይዞራሉ፥ እንደ ርስታቸውም መጠን ይጽፉታል፤ ወደ እኔም ይመለሳሉ።

5፤ በሰባትም ክፍል ይከፍሉታል፤ ይሁዳ በደቡብ በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣል፤ የዮሴፍ ወገኖች በሰሜን በኩል በዳርቻው ውስጥ ይቀመጣሉ።

6፤ እናንተም ምድሩን በሰባት ክፍል ጻፉት፥ የጻፋችሁትንም ወዲህ አምጡልኝ፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት በዚህ ዕጣ አጣጥላችኋለሁ።

7፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ክህነት ርስታቸው ነውና ለሌዋውያን በመካከላችሁ እድል ፈንታ የላቸውም፤ ጋድም ሮቤልም የምናሴም ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ማዶ በምሥራቅ በኩል የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ የሰጣቸውን ርስታቸውን ተቀብለዋል።

8፤ ሰዎችም ተነሥተው ሄዱ፤ ኢያሱም ምድሩን ሊጽፉ የሄዱትን። ሂዱ፥ ምድሩንም ዞራችሁ ጻፉት፥ ወደ እኔም ተመለሱ፤ በዚህም በሴሎ በእግዚአብሔር ፊት ዕጣ አጣጥላችኋለሁ ብሎ አዘዛቸው።

9፤ ሰዎቹም ሄደው ምድሩን ዞሩ፥ እንደ ከተሞችም በሰባት ክፍል ከፈሉት፥ በመጽሐፍም ጻፉት፤ ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ሴሎ ተመለሱ።

10፤ ኢያሱም በእግዚአብሔር ፊት በሴሎ ዕጣ አጣጣላቸው፤ በዚያም ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች እንደ ክፍሎቻቸው ምድሩን ከፈለ።

11፤ የብንያምም ልጆች ነገድ ዕጣ በየወገኖቻቸው ወጣ፤ የዕጣቸውም ዳርቻ በይሁዳ ልጆችና በዮሴፍ ልጆች መካከል ወጣ።

12፤ በሰሜን በኩል ድንበራቸው ከዮርዳኖስ ጀመረ፤ ድንበሩም ወደ ኢያሪኮ ወደ ሰሜን ወገን ወጣ፥ ከዚያም በተራራማው አገር ወደ ምዕራብ ወጣ፥ መውጫውም በቤትአዌን ምድረ በዳ ነበረ።

13፤ ድንበሩም ከዚያ በደቡብ በኩል ቤቴል ወደምትባል ወደ ሎዛ አለፈ፤ ድንበሩም በታችኛው ቤትሖሮን በደቡብ በኩል ባለው ተራራ ወደ አጣሮትአዳር ወረደ።

14፤ ድንበሩም ወደ ምዕራብ ሄደ፥ በቤትሖሮንም ፊት ለፊት ካለው ተራራ ወደ ደቡብ ዞረ፤ መውጫውም ቂርያትይዓሪም በምትባል በይሁዳ ልጆች ከተማ በቂርያትበኣል ነበረ፤ ይህ የምዕራቡ ዳርቻ ነበረ።

15፤ የደቡብም ዳርቻ ከቂርያትይዓሪም መጨረሻ ነበረ፤ ድንበሩም በምዕራብ በኩል ወደ ነፍቶ ውኃ ምንጭ ወጣ።

16፤ ድንበሩም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ፊት ለፊት ወዳለው ተራራ መጨረሻ ወረደ፥ እርሱም በራፋይም ሸሰቆ በሰሜን በኩል ነው፤ ወደ ሄኖም ሸለቆ ወደ ኢያቡስ ዳር በደቡብ በኩል ወረደ፥ ወደ ዓይንሮጌልም ወረደ።

17፤ ወደ ሰሜንም አለፈ በቤትሳሚስ ምንጭ ላይ ወጣ፥ በአዱሚም ዐቀበት ፊት ለፊት ወዳለው ወደ ጌሊሎት ደረሰ፤ ወደ ሮቤልም ልጅ ወደ ቦሀን ድንጋይ ወረደ፤

18፤ በሰሜንም ወገን ወደ ዓረባ አጠገብ አለፈ፥ ወደ ዓረባም ወረደ፤

19፤ ድንበሩም ወደ ቤትሖግላ ወደ ሰሜን ወገን አለፈ፤ መውጫውም በዮርዳኖስ መጨረሻ በደቡብ በኩል ባለው በጨው ባሕር ልሳን አጠገብ ነበረ፤ ይህ የደቡቡ ዳርቻ ነበረ።

20፤ በምሥራቅም በኩል ድንበሩ ዮርዳኖስ ነበረ። ይህ በዙርያቸው ዳርቻ በየወገኖቻቸው የብንያም ልጆች ርስት ነበረ።

21፤ የብንያምም ልጆች ነገድ ከተሞች በየወገኖቻቸው እነዚህ ነበሩ፤ ኢያሪኮ፥ ቤትሖግላ፥ ዓመቀጺጽ፥

22፤ ቤትዓረባ፥ ዘማራይም፥ ቤቴል፥

23፤24፤ ዓዊም፥ ፋራ፥ ኤፍራታ፥ ክፊርዓሞናይ፥ ዖፍኒ፥ ጋባ፤ አሥራ ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው።

25፤ ገባዖን፥ ራማ፥ ብኤሮት፥

26፤ ምጽጳ፥ ከፊራ፥ አሞቂ፥

27፤28፤ ሬቄም፥ ይርጵኤል፥ ተርአላ፥ ጼላ፥ ኤሌፍ፥ ኢየሩሳሌም የምትባል የኢያቡስ ከተማ፥ ቂርያትጊብዓት፤ አሥራ ሦስት ከተሞችና መንደሮቻቸው። የብንያም ልጆች ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።