ምዕራፍ 17።

1፤ ለምናሴ ነገድ ዕጣ ይህ ነው፤ የዮሴፍ በኵር እርሱ ነውና። የምናሴም በኵር የገለዓድ አባት ማኪር ብርቱ ሰልፈኛ ስለ ነበረ ገለዓድንና ባሳንን ወረሰ።

2፤ ዕጣውም ለቀሩት ለምናሴ ልጆች በየወገኖቻቸው፥ ለአቢዔዝር ልጆች፥ ለኬሌግ ልጆች፥ ለአሥሪኤል ልጆች፥ ለሴኬም ልጆች፥ ለኦፌር ልጆች፥ ለሸሚዳ ልጆች ሆነ፤ የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ወንዶች ልጆች በየወገኖቻቸው እነዚህ ናቸው።

3፤ ለምናሴ ልጅ፥ ለማኪር ልጅ፥ ለገለዓድ ልጅ፥ ለኦፌር ልጅ፥ ለሰለጰዓድ ግን ሴቶች ልጆች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም የሴቶች ልጆቹም ስም ማህለህ፥ ኑዓ፥ ዔግላ፥ ሚልካ፥ ቲርጻ ነበረ።

4፤ እነርሱም ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛርና ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ ወደ አለቆችም ቀርበው። እግዚአብሔር በወንድሞቻችን መካከል ርስት እንዲሰጠን ሙሴን አዘዘ አሉ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘ በአባታቸው ወንድሞች መካከል ርስት ሰጣቸው።

5፤ በዮርዳኖስ ማዶ ካለው ከገለዓድና ከባሳን አገር ሌላ ለምናሴ አሥር ዕጣ ሆነ፤

6፤ የምናሴ ሴቶች ልጆች በወንዶች ልጆች መካከል ርስት ተቀብለዋልና፤ የገለዓድም ምድር ለቀሩት ለምናሴ ልጆች ሆኖአልና።

7፤ የምናሴም ድንበር ከአሴር ጀምሮ በሴኬም ፊት ልፊት እስካለው እስከ ሚክምታት ድረስ ነበረ፤ ድንበሩም በቀኝ በኩል ወደ ዓይንታጱዋ ሰዎች አለፈ።

8፤ የታጱዋ ምድር ለምናሴ ነበረ፤ በምናሴ ዳርቻ ያለው ታጱዋ ግን ለኤፍሬም ልጆች ሆነ።

9፤ ድንበሩም ወደ ቃና ወንዝ ከወንዙ በደቡብ ወገን ወረደ፤ በምናሴም ከተሞች መካከል የነበሩት እነዚህ ከተሞች ለኤፍሬም ሆኑ፤ የምናሴም ድንበር በወንዙ በኩል በሰሜን ወገን ነበረ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ።

10፤ በደቡብ በኩል ያለው ለኤፍሬም ነበረ፥ በሰሜንም በኩል ያለው ለምናሴ ነበረ፥ ድንበሩም ባሕሩ ነበረ፤ በሰሜን በኩል ወደ አሴር፥ በምሥራቅም በኩል ወደ ይሳኮር ደረሰ።

11፤ በይሳኮርና በአሴር መካከል ቤትሳንና መንደሮችዋ፥ ይብልዓምና መንደሮችዋ፥ ዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ዓይንዶርና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ታዕናክና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ መጊዶና የመንደሮችዋ ሰዎች፥ ሦስቱ ኮረብቶች ለምናሴ ነበሩ።

12፤ የምናሴ ልጆች ግን የእነዚህን ከተሞች ሰዎች ሊያሳድዱአቸው አልቻሉም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ።

13፤ የእስራኤልም ልጆች በጸኑ ጊዜ ከነዓናውያንን የጕልበት ግብር አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላሳደዱአቸውም።

14፤ የዮሴፍ ልጆች ኢያሱን። እኔ ብዙ ሕዝብ ስለ ሆንሁ እስከ አሁንም እግዚአብሔር ስለ ባረከኝ ለምን አንድ ክፍል አንድም ዕጣ ብቻ ርስት አድርገህ ሰጠኸኝ? አሉት።

15፤ ኢያሱም። ብዙ ሕዝብስ ከሆንህ ተራራማውም የኤፍሬም አገር ጠብቦህ እንደ ሆነ ወደ ዱር ወጥተህ በፌርዛውያንና በራፋይም ምድር ለአንተ ስፍራ መንጥር አላቸው።

16፤ የዮሴፍም ልጆች። ተራራማው አገር አይበቃንም፤ በሸለቆውም ውስጥ ለሚኖሩት፥ በቤትሳንና በመንደሮችዋ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ለሚኖሩት ከነዓናውያን የብረት ሰረገሎች አላቸው አሉት።

17፤ ኢያሱም የዮሴፍ ወገን ለሚሆኑ ለኤፍሬምና ለምናሴ። አንተ ብዙ ሕዝብ ነህ፥ ጽኑም ኃይል አለህ አንድ ዕጣ ብቻ አይሆንልህም፤

18፤ ነገር ግን ተራራማው አገር ለአንተ ይሆናል፥ ዱር እንኳን ቢሆንም ትመነጥረዋለህ፥ ለአንተም ይሆናል፤ ለከነዓናውያንም የብረት ሰረገሎች ቢሆኑላቸው የበረቱም ቢሆኑ ታሳድዳቸዋለህ አላቸው።