ምዕራፍ 14።

1፤ የእስራኤልም ልጆች በከነዓን ምድር የወረሱት፥ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ የእስራኤልም ልጆች ነገድ የአባቶቻቸው አለቆች ያካፈሉአቸው ርስት ይህ ነው፤

2፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ እንዳዘዘ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው በየርስታቸው በዕጣ አካፈሉአቸው።

3፤ ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዮርዳኖስ ማዶ ሙሴ ርስት ሰጥቶ ነበረ፤ ነገር ግን በመካከላቸው ለሌዋውያን ርስት አልሰጣቸውም።

4፤ የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ነበሩ፤ ለሌዋውያንም ከሚቀመጡባቸው ከተሞች ለእንስሶቻቸውና ለከብቶቻቸውም ከሚሆን መሰምርያቸው በቀር በምድሩ ውስጥ ድርሻ አልሰጡአቸውም።

5፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፥ ምድሪቱንም ተካፈሉ።

6፤ የይሁዳም ልጆች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ቄኔዛዊውም የዮፎኒ ልጅ ካሌብ አለው። ለአምላክህ ሰው ለሙሴ ስለ እኔና ስለ አንተ እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ የተናገረውን ነገር ታውቃለህ።

7፤ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድርን እሰልል ዘንድ ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ እኔ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ እኔም በልቤ የነበረውን ቃል መለስሁለት።

8፤ ከእኔ ጋር የወጡ ወንድሞቼ ግን የሕዝቡን ልብ አቀለጡ፤ እኔ ግን አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽሜ ተከተልሁ።

9፤ ሙሴም በዚያ ቀን። አምላኬን እግዚአብሔርን ፈጽመህ ተከትለሃልና እግርህ የረገጠው ምድር ለአንተና ለልጆችህ ለዘላለም በእርግጥ ርስት ይሆናል ብሎ ማለ።

10፤ አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር ለሙሴ ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ፥ እስራኤል በምድረ በዳ ሲዞሩ፥ እርሱ እንደ ተናገረኝ እግዚአብሔር እነዚህን አርባ አምስት ዓመት በሕይወት አኖረኝ፤ አሁንም፥ እነሆ፥ ለእኔ ዛሬ ሰማንያ አምስት ዓመት ሆነኝ።

11፤ ሙሴም በላከኝ ጊዜ እንደ ነበርሁ፥ ዛሬ ጕልበታም ነኝ፤ ጕልበቴም በዚያን ጊዜ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ ዛሬ ለመዋጋት ለመውጣትም ለመግባትም ጉልበቴ ያው ነው።

12፤ አሁን እንግዲህ በዚያን ቀን እግዚአብሔር የተናገረውን ይህን ተራራማ አገር ስጠኝ፤ አንተ በዚያ ቀን ዔናቃውያን ታላላቆችና የተመሸጉ ከተሞችም በዚያ እንዳሉ ሰምተህ ነበር፤ ምናልባት እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ይሆናል፥ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረኝ አሳድዳቸዋለሁ።

13፤ ኢያሱም ባረከው፤ ለዮፎኒም ልጅ ለካሌብ ኬብሮንን ርስት አድርጎ ሰጠው።

14፤ ስለዚህም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ፈጽሞ ስለ ተከተለ ኬብሮን እስከ ዛሬ ለቄኔዛዊው ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ርስት ሆነች።

15፤ የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያትአርባቅ ትባል ነበር፤ ይህም አርባቅ በዔናቅ ሰዎች መካከል ከሁሉ ከፍ ያለ ነበረ። ምድሪቱም ከውጊያ ዐረፈች። a