ምዕራፍ 38።

1፤ እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ።

2፤ ያለ እውቀት በሚነገር ቃል

ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው?

3፤ እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤

እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።

4፤ ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ?

ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር።

5፤ ብታውቅስ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥

በላይዋስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው?

6፤7፤ አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥

የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥

መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር?

የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?

8፤ ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ

ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው?

9፤ ደመናውን ለልብሱ፥

ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፤

10፤ ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥

መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ።

11፤ እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፤

በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ።

12፤13፤ የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥

ከእርስዋም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥

በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘሃልን?

ለወገግታም ስፍራውን አስታወቀኸዋልን?

14፤ ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁ እርስዋ ትለወጣለች፤

ነገርም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል።

15፤ ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥

ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል።

16፤ ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን?

በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን?

17፤ የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን?

የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን?

18፤ ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን?

ሁሉን አውቀህ እንደ ሆነ ተናገር።

19፤20፤ ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥

ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥

የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው?

የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ?

21፤ በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥

የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፤

በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም።

22፤ በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን?

የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን?

23፤ ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው።

24፤ ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፈላል?

የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል?

25፤26፤ ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥

27፤ ሣሩንም እንዲያበቅል፥

ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥

ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብን ያዘንብ ዘንድ፥

ለፈሳሹ ውኃ መንዶልዶያውን፥

ወይስ ለሚያንጐደጕድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው?

28፤ በውኑ ለዝናብ አባት አለውን?

ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው?

29፤ በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ?

የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው?

30፤ ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥

የቀላዩም ፊት ረግቶአል።

31፤ በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥

ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን?

32፤ ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥

ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን?

33፤ የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን?

በምድርስ ለይ እንዲሠለጥን ልታደርግ ትችላለህን?

34፤ የውኆች ብዛት ይሸፍንህ ዘንድ

ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን?

35፤ መብረቆች ሄደው። እነሆ፥ እዚህ አለን ይሉህ ዘንድ

ልትልካቸው ትችላለህን?

36፤ በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥

ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው?

37፤38፤ የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው?

ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥

ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥

የሰማይን ረዋት ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው?

39፤40፤ በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥

በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥

ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን?

የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን?

41፤ ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥

የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥

ለቍራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?