ምዕራፍ 37።

1፤ ስለዚህም ልቤ ተንቀጠቀጠ፥

ከስፍራውም ተንቀሳቀሰ።

2፤ የድምፁን መትመም ስሙ፥

ከአፉም የሚወጣውን ጕርምርምታ አድምጡ።

3፤ እርሱን ወደ ሰማያት ሁሉ ታች፥

ብርሃኑንም ወደ ምድር ዳርቻ ይሰድዳል።

4፤ በስተ ኋላው ድምፅ ይጮኻል፤

በግርማውም ድምፅ ያንጐደጕዳል፤

ድምፁም በተሰማ ጊዜ

መብረቁን አይከለክልም።

5፤ እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅኛ ያንጐደጕዳል፤

እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር ያደርጋል።

6፤ በረዶውንና ውሽንፍሩን ብርቱንም ዝናብ።

በምድር ላይ ውደቁ ይላል።

7፤ ሰው ሁሉ ሥራውን ያውቅ ዘንድ

የሰውን ሁሉ እጅ ያትማል።

8፤ አውሬዎቹም ወደ ጫካው ይገባሉ፥

በዋሾቻቸውም ይቀመጣሉ።

9፤ ከተሰወረ ማደሪያውም ዐውሎ ነፋስ፥

ከሰሜንም ብርድ ይወጣል።

10፤ ከእግዚአብሔር እስትንፋስ ውርጭ ተሰጥቶአል፤

የውኆችም ስፋት ይጠብባል።

11፤ የውኃውንም ሙላት በደመና ላይ ይጭናል፤

የብርሃኑንም ደመና ይበታትናል፤

12፤13፤ ለተግሣጽ ወይም ለምድሩ ወይም ለምሕረት ቢሆን፥

ሰው በሚኖርበት ዓለም ላይ

ያዘዘውን ሁሉ ያደርግ ዘንድ

ፈቃዱ ወደ መራችው ይዞራል።

14፤ ኢዮብ ሆይ፥ ይህን ስማ፤

ቁም፥ የእግዚአብሔርንም ተአምራት አስብ።

15፤ በውኑ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያዝዛቸው፥

የደመናውንም ብርሃን እንዴት እንደሚያበራ አውቀሃልን?

16፤ ወይስ የደመናውን ሚዛን፥

ወይስ በእውቀት ፍጹም የሆነውን ተአምራት አውቀሃልን?

17፤ በደቡብ ነፋስ ምድር ጸጥ ባለች ጊዜ፥

ልብስህ የሞቀች አንተ ሆይ፥

18፤ እንደ ቀለጠ መስተዋት

ብርቱ የሆኑትን ሰማያት ከእርሱ ጋር ልትዘረጋ ትችላለህን?

19፤ እኛ ከጨለማ የተነሣ በሥርዓት መናገር አንችልምና

የምንለውን አስታውቀን።

20፤ ማንም በእርሱ ላይ ቢናገር ፈጽሞ ይዋጣልና

እኔ እናገር ዘንድ ብወድድ ሰው ይነግረዋልን?

21፤ አሁንም ነፋስ አልፎ ካጠራቸው በኋላ፥

ሰው በሰማያት የሚበራውን ብርሃን ሊመለከት አይችልም።

22፤ ከሰሜን ወርቅ የሚመስል ጌጠኛ ብርሃን ይወጣል፤

በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስፈራ ግርማ አለ።

23፤ ሁሉን የሚችል አምላክን እናገኝ ዘንድ አንችልም፤

በኃይል ታላቅ ነው፤

በፍርድና በጽድቅም አያስጨንቅም።

24፤ ስለዚህ ሰዎች ይፈሩታል፤

በልባቸውም ጠቢባን የሆኑትን ሁሉ አይመለከትም።