ምዕራፍ 21።

1፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ።

2፤ ስሙ፥ ቃሌን ስሙ፤

ይህም መጽናናታችሁ ይሁን።

3፤ እናገር ዘንድ ተዉኝ፤

ከተናገርሁም በኋላ ተሳለቁ።

4፤ በውኑ የኀዘን እንጉርጕሮዬ ለሰው እናገራለሁን?

አለመታገሥ ስለ ምን አይገባኝም?

5፤ ወደ እኔ ተመልከቱ፥ ተደነቁም፤

እጃችሁንም በአፋችሁ ላይ አኑሩ።

6፤ እኔ ባሰብሁ ቍጥር እጨነቃለሁ፥

ፃዕርም ሥጋዬን ይይዛል።

7፤ ስለ ምን ኃጢአተኞች በሕይወት ይኖራሉ?

ስለ ምንስ ያረጃሉ? በባለጠግነትስ ስለ ምን ይበረታሉ?

8፤ ዘራቸው ከእነርሱ ጋር ጸንቶ ይኖራል፥

ልጆቻቸውም በዓይናቸው ፊት ናቸው።

9፤ ቤታቸው ከፍርሃት ወጥቶ የታመነ ነው፥

የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።

10፤ ኮርማቸው ይወልዳል፥ ዘሩንም አይጥለውም፤

ላማቸውም ትወልዳለች፥ አትጨነግፍም።

11፤ ሕፃናቶቻቸውን እንደ መንጋ ያወጣሉ፥

ልጆቻቸውም ይዘፍናሉ።

12፤ ከበሮና መሰንቆ ወስደው ይዘምራሉ፥

በእምቢልታ ድምፅ ደስ ይላቸዋል።

13፤ ዕድሜያቸውንም በተድላ ይፈጽማሉ፤

ድንገትም ወደ ሲኦል ይወርዳሉ።

14፤ እግዚአብሔርንም። ከእኛ ዘንድ ራቅ፤

መንገድህን እናውቅ ዘንድ አንወድድም።

15፤ እናመልከውስ ዘንድ ሁሉን የሚችል አምላክ ማን ነው?

ወይስ ወደ እርሱ ብንጸልይ ምን ይጠቅመናል? ይላሉ።

16፤ እነሆ፥ ሀብታቸው በእጃቸው ውስጥ አይደለምን?

የኃጥአን ምክር ከእኔ ዘንድ የራቀች ናት።

17፤ የኃጥአን መብራት የጠፋው፥

መቅሠፍትም የመጣባቸው፥

እግዚአብሔርም በቍጣው መከራ የከፈላቸው፥

18፤ በነፋስ ፊት እንደ ገለባ፥

ዐውሎ ነፋስም እንደሚወስደው ትቢያ የሆኑ ስንት ጊዜ ነው?

19፤ እናንተ። እግዚአብሔር በደላቸውን ለልጆቻቸው ይጠብቃል ብላችኋል።

እነርሱ ያውቁ ዘንድ ፍዳን ለራሳቸው ይክፈል።

20፤ ዓይኖቻቸው ጥፋታቸውን ይዩ፥

ሁሉን ከሚችል አምላክ ቍጣ ይጠጡ።

21፤ የወራታቸውስ ቍጥር ቢቈረጥ፥

ከእነርሱ በኋላ የቤታቸው ደስታ ምን ይሆናቸዋል?

22፤ ከፍ ከፍ ባሉትስ ላይ ለሚፈርድ ለእግዚአብሔር

በውኑ ሰው እውቀትን ያስተምራልን?

23፤ አንድ ሰው በሰላም ተዘልሎ ሲቀመጥ

በሙሉ ኃይሉ ሳለ ይሞታል።

24፤ በአንጀቱ ውስጥ ስብ ሞልቶአል፥

የአጥንቶቹም ቅልጥም ረጥቦአል።

25፤ ሌላውም ሰው መልካምን ነገር ከቶ ሳይቀምስ

በተመረረች ነፍስ ይሞታል።

26፤ በአፈር ውስጥ በአንድ ላይ ይተኛሉ፥

ትልም ይከድናቸዋል።

27፤ እነሆ፥ አሳባችሁን፥

የመከራችሁብኝንም ክፉ ምክር አውቄዋለሁ።

28፤ እናንተ። የከበርቴው ቤት የት ነው?

ኃጢአተኛውም ያደረበት ድንኳን የት ነው? ብላችኋል።

29፤ መንገድ አላፊዎችን አልጠየቃችሁምን?

ምልክታቸውን አታውቁምን?

30፤ ኃጢአተኛው በመቅሠፍት ቀን እንደ ተጠበቀ፥

በቍጣው ቀን እንደሚድን።

31፤ መንገዱን በፊቱ የሚናገር ማን ነው?

የሠራውንስ የሚመልስበት ማን ነው?

32፤ እርሱን ግን ወደ መቃብር ይሸከሙታል፥

ሰዎቹም በመቃብሩ ላይ ይጠብቃሉ።

33፤ የሸለቆው ጓል ይጣፍጥለታል፤

በኋላውም ሰው ሁሉ ይሳባል፥

በፊቱም ቍጥር የሌለው ጉባኤ አለ።

34፤ የምትመልሱልኝ ውስልትና ነውና

በከንቱ እንዴት ታጽናኑኛላችሁ?