ምዕራፍ 20።

1፤ ናዕማታዊውም ሶፋር መለሰ እንዲህም አለ።

2፤ ስለዚህ በውስጤ ስላለው ችኰላ አሳቤ ትመልስልኛለች።

3፤ የሚያሳፍረኝንም ተግሣጽ ሰምቻለሁ፥

የማስተዋሌም መንፈስ ይመልስልኛል።

4፤ ሰው በምድር ላይ ከተቀመጠ፥ ከዱሮ ዘመን ጀምሮ፥

5፤ የኃጢአተኛ ፉከራ አጭር መሆኑን

የዝንጉዎችም ደስታ ቅጽበት መሆኑን አታውቁምን?

6፤ ከፍታው ወደ ሰማይ ቢወጣ፥

ራሱም እስከ ደመና ቢደርስ፥

7፤ እንደ ፋንድያ ለዘላለም ይጠፋል፤

ያዩትም። ወዴት ነው? ይላሉ።

8፤ እንደ ሕልም ይበርራል፥ እርሱም አይገኝም፤

እንደ ሌሊትም ራእይ ይሰደዳል።

9፤ ያየችውም ዓይን ዳግመኛ አታየውም፤

ስፍራውም ከእንግዲህ ወዲህ አይመለከተውም።

10፤ ልጆቹ ድሆቹን ያቈላምጣሉ፤

እጁ ሀብቱን ይመልሳል።

11፤ አጥንቶቹ ብላቴንነቱን ሞልተዋል፤

ነገር ግን ከእርሱ ጋር በመሬት ውስጥ ይተኛል።

12፤ ክፋት በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፥

ከምላሱም በታች ቢሰውረው፥

13፤ ቢጠብቀውም ባይተወውም፥

በጕሮሮውም ቢይዘው፥

14፤ መብሉ በአንጀቱ ውስጥ ይገላበጣል፤

እንደ እፉኝትም ሐሞት በውስጡ ይሆናል።

15፤ የዋጠውን ሀብት ይተፋዋል፤

እግዚአብሔርም ከሆዱ ውስጥ ያወጣዋል።

16፤ የእፉኝትን መርዝ ይጠባል፤

የእባብም ምላስ ይገድለዋል።

17፤ የማሩንና የቅቤውን ፈሳሽ

ወንዞቹንም አይመለከትም።

18፤ የድካሙን ፍሬ ሳይውጠው ይመልሰዋል፤

እንደ ንግዱም ትርፍ አይደሰትም።

19፤ ድሀውን አስጨንቆአል፥ ትቶታልም፤

ያልሠራውንም ቤት በዝብዞአል።

20፤ ሆዱ ዕረፍትን አላወቀምና

የወደደው ነገር አላዳነውም።

21፤ እርሱ ከበላ በኋላ ምንም አልተረፈም፤

ስለዚህ በረከቱ አይከናወንለትም።

22፤ በጠገበ ጊዜ ይጨነቃል፤

የችግረኞችም ሁሉ እጅ ታገኘዋለች።

23፤ ሆዱን ሳያጠግብ

እግዚአብሔር የቍጣውን ትኵሳት ይሰድድበታል፥

ሲበላም ያዘንብበታል።

24፤ ከብረት መሣርያም ይሸሻል፥

የናስም ቀስት ይወጋዋል።

25፤ እርሱም ይመዝዘዋል፥ ከሥጋውም ይወጣል፤

ከሐሞቱም ብልጭ ብሎ ይሠርጻል፤

ፍርሃትም ይወድቅበታል።

26፤ ጨለማ ሁሉ ስለ ከበረው ዕቃ ተዘጋጅቶአል፤

በሰው አፍ እፍ የማትባል እሳት ትበላዋለች፤

በድንኳኑ ውስጥ የቀረው ይጨነቅባታል።

27፤ ሰማይ ኃጢአቱን ይገልጥበታል፥

ምድርም ትነሣበታለች።

28፤ የቤቱም ባለጠግነት ይሄዳል፤

በቍጣው ቀን እንደ ፈሳሽ ውኃ ያልፋል።

29፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የበደለኛ ሰው እድል ፈንታ፥

ከእግዚአብሔርም የተመደበ ርስቱ ይህ ነው።