ምዕራፍ 3።

1፤ ከዚያም በኋላ ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ።

2፤ ኢዮብም መለሰ እንዲህ አለ።

3፤ ያ የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፥

ያም። ወንድ ልጅ ተፀነሰ የተባለበት ሌሊት።

4፤ ያ ቀን ጨለማ ይሁን፤

እግዚአብሔር ከላይ አይመልከተው፥

ብርሃንም አይብራበት።

5፤ ጨለማና የሞት ጥላ የራሳቸው ገንዘብ ያድርጉት፤

ዳመናም ይረፍበት፤

የቀን ጨለማ ሁሉ ያስፈራው።

6፤ ያን ሌሊት ጨለማ ይያዘው፤

በዓመቱ ቀኖች መካከል ደስ አይበለው፤

በወሮች ውስጥ ገብቶ አይቈጠር።

7፤ እነሆ፥ ያ ሌሊት መካን ይሁን፤

እልልታ አይግባበት።

8፤ ሌዋታንን ለማንቀሳቀስ የተዘጋጁ

ቀኑን የሚረግሙ ይርገሙት።

9፤ አጥቢያ ኮከቦች ይጨልሙ፤

ብርሃንን ቢጠባበቅ አያግኘው፥

የንጋትንም ቅንድብ አይይ፤

10፤ የእናቴን ማኅፀን ደጅ አልዘጋምና፥

መከራንም ከዓይኔ አልሰወረምና።

11፤ በማኅፀን ሳለሁ ስለ ምን አልሞትሁም?

ከሆድስ በወጣሁ ጊዜ ፈጥኜ ስለ ምን አልጠፋሁም?

12፤ ጕልበቶች ስለ ምን ተቀበሉኝ?

ጡትስ ስለ ምን ጠባሁ?

13፤ አሁን ተኝቼ ዝም ባልሁ ነበር፤

አንቀላፍቼ ባረፍሁ ነበር፤

14፤ የፈረሰውን ለራሳቸው ከሚሠሩት

ከምድር ነገሥታትና መካሮች ጋር፥

15፤ ወይም ቤታቸውን ብር ከሞሉ

ወርቅም ካላቸው መኳንንት ጋር፥

16፤ ወይም እንደ ተቀበረ ጭንጋፍ፥

ብርሃንም እንዳላዩ ሕፃናት በሆንሁ ነበር።

17፤ ክፉዎች በዚያ መናደዳቸውን ይተዋሉ፤

በዚያም ደካሞች ያርፋሉ።

18፤ በዚያ ግዞተኞች በአንድነት ተዘልለው ተቀምጠዋል፤

የአስጨናቂውን ድምፅ አይሰሙም።

19፤ ታናሽና ታላቅ በዚያ አሉ፤

ባሪያም ከጌታው ነጻ ወጥቶአል።

20፤ በመከራ ላሉት ብርሃን፥

ነፍሳቸው መራራ ለሆነችባቸው፥

21፤ የተሰወረ ሀብትን ከሚቈፍሩ ይልቅ

ሞትን ለሚጠብቁ ለማያገኙትም፥

22፤ መቃብርን ባገኙ ጊዜ

በእልልታ ደስ ለሚላቸው፥ ሐሤትንም ለሚያደርጉ

ሕይወት ስለ ምን ተሰጠ?

23፤ መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፥

እግዚአብሔርም በአጥር ላጠረው

ብርሃን ስለ ምን ተሰጠ?

24፤ ከእንጀራዬ በፊት ልቅሶዬ መጥቶአልና፥

ጩኸቴም እንደ ውኃ ፈስሶአል።

25፤ የፈራሁት ነገር መጥቶብኛልና፥

የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል።

26፤ ተዘልዬ አልተቀመጥሁም፥ አልተማመንሁም፥ አላረፍሁም፤

ነገር ግን መከራ መጣብኝ።