ምዕራፍ 24

1 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳን ንጉሥ የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን የይሁዳንም አለቆች ጠራቢዎችንና ብረት ሠራተኞችን ከኢየሩሳሌም ማርኮ ወደ ባቢሎን ካፈለሳቸው በኋላ፥ እግዚአብሔር አሳየኝ፥ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መቅደስ ፊት ሁለት ቅርጫት በለስ ተቀምጠው ነበር።

2 በአንደኛይቱ ቅርጫት አስቀድሞ እንደ ደረሰ በለስ የሚመስል እጅግ መልካም በለስ ነበረባት፤ በሁለተኛይቱ ቅርጫት ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ በለስ ነበረባት።

3 እግዚአብሔርም። ኤርምያስ ሆይ፥ የምታየው ምንድር ነው? አለኝ። እኔም። በለስን አያለሁ፤ እጅግ መልካም የሆነ መልካም በለስ፥ ከክፋቱም የተነሣ ይበላ ዘንድ የማይቻል እጅግ ክፉ የሆነ ክፉ በለስ ነው አልሁ።

4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

5 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እንደዚህ እንደ መልካሙ በለስ፥ እንዲሁ ከዚህ ስፍራ ወደ ከለዳውያን ምድር የሰደድሁትን የይሁዳን ምርኮ ለበጐነት እመለከተዋለሁ።

6 ዓይኔንም ለበጐነት በእነርሱ ላይ አደርጋለሁ ወደዚህችም ምድር እመልሳቸዋለሁ፤ እሠራቸዋለሁ እንጂ አላፈርሳቸውም፤ እተክላቸዋለሁ እንጂ አልነቅላቸውም።

7 እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ የሚያውቅ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በፍጹምም ልባቸው ወደ እኔ ይመለሳሉና ሕዝብ ይሆኑኛል እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ።

8 እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል። ከክፋቱ የተነሣ ይበላ ዘንድ እንደማይቻል እንደ ክፉው በለስ፥ እንዲሁ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን አለቆቹንም በዚህችም አገር የሚቀሩትን የኢየሩሳሌም ቅሬታ በግብጽም አገር የሚቀመጡትን እጥላቸዋለሁ።

9 በማሳድዳቸውም ስፍራ ሁሉ ለስድብና ለምሳሌ ለማላገጫና ለእርግማን ይሆኑ ዘንድ በምድር መንግሥታት ሁሉ ለመበተን አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።

10 ለእነርሱና ለአባቶቻቸውም ከሰጠኋቸው ምድር እስኪጠፉ ድረስ በመካከላቸው ሰይፍንና ራብን ቸነፈርንም እሰድዳለሁ።