ምዕራፍ 11።

1፤ ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ጽኑዕ ኃያል ሰው የጋለሞታ ሴትም ልጅ ነበረ። ገለዓድም ዮፍታሔን ወለደ።

2፤ የገለዓድም ሚስት ወንዶች ልጆችን ወለደችለት፤ ልጆችዋም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን። የልዩ ሴት ልጅ ነህና በአባታችን ቤት አትወርስም ብለው አሳደዱት።

3፤ ዮፍታሔም ከወንድሞቹ ፊት ሸሽቶ በጦብ ምድር ተቀመጠ፤ ምናምንቴዎችም ሰዎች ተሰብስበው ዮፍታሔን ተከተሉት።

4፤ ከዚያም ወራት በኋላ የአሞን ልጆች ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ነበር።

5፤ የአሞንም ልጆች ከእስራኤል ጋር በተዋጉ ጊዜ የገለዓድ ሽማግሌዎች ዮፍታሔን ከጦብ ምድር ለማምጣት ሄዱ።

6፤ ዮፍታሔንም። ና፥ ከአሞን ልጆች ጋር እንድንዋጋ አለቃችን ሁን አሉት።

7፤ ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። የጠላችሁኝ ከአባቴም ቤት ያሳደዳችሁኝ እናንተ አይደላችሁምን? አሁን በተጨነቃችሁ ጊዜ ለምን ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው።

8፤ የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። ከእኛ ጋር እንድትወጣ፥ ከአሞንም ልጆች ጋር እንድትዋጋ፥ ስለዚህ አሁን ወደ አንተ ተመልሰን መጣን፤ በገለዓድም ሰዎች ሁሉ ላይ አለቃችን ትሆናለህ አሉት።

9፤ ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች። ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው፥ እኔ አለቃችሁ እሆናለሁን? አላቸው።

10፤ የገለዓድም ሽማግሌዎች ዮፍታሔን። እግዚአብሔር በመካከላችን ምስክር ይሁን፤ በእርግጥ እንደ ቃልህ እናደርጋለን አሉት።

11፤ ዮፍታሔም ከገለዓድ ሽማግሌዎች ጋር ሄደ፥ ሕዝቡም በላያቸው ራስና አለቃ አደረጉት፤ ዮፍታሔም ቃሉን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት በምጽጳ ተናገረ።

12፤ ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ። አገሬን ለመውጋት ወደ እኔ የምትመጣ አንተ ከእኔ ጋር ምን አለህ? ብሎ መልክተኞችን ላከ።

13፤ የአሞንም ልጆች ንጉሥ የዮፍታሔን መልክተኞች። እስራኤል ከግብፅ በወጣ ጊዜ ከአርኖን ጀምሮ እስከ ያቦቅና እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ምድሬን ስለ ወሰደ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ ብሎ መለሰላቸው።

14፤ ዮፍታሔም ወደ አሞን ልጆች ንጉሥ መልክተኞችን እንደ ገና ላከ፥

15፤ እንዲህም አለው። ዮፍታሔ እንዲህ ይላል። እስራኤል የሞዓብን ምድር የአሞንንም ልጆች ምድር አልወሰደም፤

16፤ ነገር ግን ከግብፅ በወጣ ጊዜ፥ እስራኤልም በምድረ በዳ በኩል ወደ ኤርትራ ባሕር በሄደ ጊዜ፥ ወደ ቃዴስም በደረሰ ጊዜ፥

17፤ እስራኤል ወደ ኤዶምያስ ንጉሥ። በምድርህ እንዳልፍ፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ ብሎ መልክተኞችን ላከ፤ የኤዶምያስም ንጉሥ አልሰማም። እንዲሁም ወደ ሞዓብ ንጉሥ ላከ፥ እርሱም አልፈቀደም።

18፤ እስራኤልም በቃዴስ ተቀመጠ። በምድረ በዳም በኩል ሄዱ፥ የኤዶምያስንና የሞዓብንም ምድር ዞሩ፤ ከሞዓብ ምድርም በምሥራቅ በኩል መጡ በአርኖንም ማዶ ሰፈሩ፤ አርኖንም የሞዓብ ድንበር ነበረና የሞዓብን ድንበር አላለፉም።

19፤ እስራኤልም ወደ አሞራዊው ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልክተኞችን ላከ፤ እስራኤልም። በምድርህ በኩል ወደ ስፍራችን፥ እባክህ፥ አሳልፈን አለው።

20፤ ሴዎንም እስራኤል በድንበሩ እንዲያልፍ አላመነውም ነበር፤ ነገር ግን ሴዎን ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ በያሀጽም ሰፈረ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ።

21፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፥ መቱአቸውም፤ እስራኤልም በዚያ ምድር ተቀምጠው የነበሩትን የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሰ።

22፤ ከአርኖንም እስከ ያቦቅ ድረስ ከምድረ በዳውም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ የአሞራውያንን ምድር ሁሉ ወረሱ።

23፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሞራውያንን አስወገደ፤ አንተም ምድሩን ትወርሳለህን?

24፤ አምላክህ ካሞሽ የሚሰጥህን አትወርስምን? እኛም አምላካችን እግዚአብሔር ከፊታችን ያስወጣቸውን የእነርሱን ምድር እንወርሳለን።

25፤ ወይስ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ አንተ ትሻላለህን? በውኑ እርሱ እስራኤልን ከቶ ተጣላውን? ወይስ ተዋጋውን?

26፤ እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮችዋ፥ በአሮዔርና በመንደሮችዋ፥ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረ ጊዜ፥ በዚያ ዘመን ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር?

27፤ እኔ አልበደልሁህም፥ አንተ ግን ከእኔ ጋር እየተዋጋህ በድለኸኛል፤ ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆችና በአሞን ልጆች መካከል ዛሬ ይፍረድ።

28፤ ነገር ግን ዮፍታሔ የላከበትን ቃል የአሞን ልጆች ንጉሥ አልሰማም።

29፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በዮፍታሔ ላይ መጣ፤ እርሱም ገለዓድንና ምናሴን አለፈ፥ በገለዓድም ያለውን ምጽጳን አለፈ፥ ከምጽጳም ወደ አሞን ልጆች አለፈ።

30፤ ዮፍታሔም። በእውነት የአሞንን ልጆች በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፥

31፤ ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና በተመለስሁ ጊዜ፥ ሊገናኘኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አቀርበዋለሁ ብሎ ለእግዚአብሔር ስእለት ተሳለ።

32፤ ዮፍታሔም ሊዋጋቸው ወደ አሞን ልጆች አለፈ፥ እግዚአብሔርም በእጁ አሳልፎ ሰጣቸው።

33፤ ከአሮዔርም እስከ ሚኒትና እስከ አቤልክራሚም ድረስ ሀያ ከተሞችን በታላቅ አገዳደል መታቸው። የአሞንም ልጆች በእስራኤል ልጆች ፊት ተዋረዱ።

34፤ ዮፍታሄም ወደ ቤቱ ወደ ምጽጳ መጣ፥ እነሆም ልጁ ከበሮ ይዛ እየዘፈነች ልትገናኘው ወጣች፤ ለእርሱም አንዲት ብቻ ነበረች፤ ከእርስዋም በቀር ወንድ ወይም ሴት ሌላ ልጅ አልነበረውም።

35፤ እርስዋንም ባየ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ። አወይ ልጄ ሆይ! ወደ እግዚአብሔር አፌን ከፍቻለሁና፥ ከዚያውም እመለስ ዘንድ አልችልምና በጣም አዋረድሽኝ አስጨነቅሽኝም አላት።

36፤ እርስዋም። አባቴ ሆይ፥ አፍህን ለእግዚአብሔር ከከፈትህ፥ እግዚአብሔር በጠላቶችህ በአሞን ልጆች ላይ ተበቅሎልሃልና በአፍህ እንደ ተናገርህ አድርግብኝ አለችው።

37፤ አባትዋንም። ይህ ነገር ይደረግልኝ፤ ከዚህ ሄጄ በተራሮች ላይ እንድወጣና እንድወርድ፥ ከባልንጀሮቼም ጋር ለድንግልናዬ እንዳለቅስ ሁለት ወር አሰናብተኝ አለችው።

38፤ እርሱም። ሂጂ አለ። ሁለት ወርም አሰናበታት፤ ከባልንጀሮችዋም ጋር ሄደች፥ በተራሮችም ላይ ለድንግልናዋ አለቀሰች።

39፤ ሁለትም ወር ከተፈጸመ በኋላ ወደ አባትዋ ተመለሰች፥ እንደ ተሳለውም ስእለት አደረገባት፤ እርስዋም ወንድ አላወቀችም ነበር።

40፤ የእስራኤልም ሴቶች ልጆች በዓመት በዓመቱ እየሄዱ የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በዓመት አራት ቀን ሙሾ እንዲያወጡ በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆነ።