ምዕራፍ 59።

1፤ እነሆ፥ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም ከመስማት አልደነቈረችም፤

2፤ ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል።

3፤ እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፥ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል።

4፤ በጽድቅ የሚጠራ በእውነትም የሚፈርድ የለም፤ በምናምንቴ ነገር ታምነዋል ሐሰትንም ተናግረዋል፤ ጕዳትን ፀንሰዋል በደልንም ወልደዋል፤

5፤ የእባብን እንቍላል ቀፈቀፉ፥ የሸረሪትንም ድር አደሩ፤ እንቍላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፥ እንቍላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል።

6፤ ድሮቻቸውም ልብስ አይሆኑላቸውም፥ በሥራቸውም አይሸፈኑም፤ ሥራቸውም የበደል ሥራ ነው፥ የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው።

7፤ እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፥ ንጹሑን ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፤ አሳባቸው የኃጢአት አሳብ ነው፥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ በመንገዳቸው አለ።

8፤ የሰላምን መንገድ አያውቁም፥ በአካሄዳቸውም ፍርድ የለም፤ መንገዳቸውን አጣምመዋል፥ የሚሄድባትም ሁሉ ሰላምን አያውቅም።

9፤ ስለዚህ ፍርድ ከእኛ ዘንድ ርቆአል፥ ጽድቅም አላገኘንም፤ ብርሃንን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ እነሆም፥ ጨለማ ሆነ፤ ጸዳልን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ ነገር ግን በጨለማ ሄድን።

10፤ እንደ ዕውሮች ወደ ቅጥሩ ተርመሰመስን፥ ዓይን እንደሌላቸው ተርመሰመስን፤ በቀትር ጊዜ በድግዝግዝታ እንዳለ ሰው ተሰናከልን፥ እንደ ሙታን በጨለማ ስፍራ ነን።

11፤ ሁላችን እንደ ድቦች እንጮኻለን፥ እንደ ርግብ እንለቃቀሳለን፤ ፍርድን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር እርሱም የለም፤ መዳንም ከእኛ ዘንድ ርቆአል።

12፤ ዓመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኃጢአታችን መስክሮብናልና፥ ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ በደላችንን እናውቃለንና።

13፤ ዐምፀናል፥ ሐሰትን ተናግረናል፥ አምላካችንንም ከመከተል ተመልሰናል፤ ግፍንና ዓመፅንም ተናግረናል፥ የኃጢአት ቃልንም ፀንሰን ከልብ አውጥተናል።

14፤ ፍርድም ወደ ኋላ ተመልሶአል፥ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፤ እውነትም በአደባባይ ላይ ወድቆአልና፥ ቅንነትም ሊገባ አልቻለምና።

15፤ እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ለብዝበዛ ሆኖአል።

እግዚአብሔርም አየ፥ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ።

16፤ ሰውም እንደሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደሌለ ተረዳ ተደነቀም፤ ስለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው።

17፤ ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ።

18፤ እንደ ሥራቸው መጠን እንዲሁ ቍጣን ለባላጋራዎቹ፥ ፍዳንም ለጠላቶቹ ይከፍላል፤ ለደሴቶችም ፍዳቸውን ይከፍላል።

19፤ እርሱ የእግዚአብሔር ነፋስ እንደሚነዳው እንደ ጐርፍ ፈሳሽ ይመጣልና በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም፥ በፀሐይ መውጫም ያሉት ክብሩን ይፈራሉ።

20፤ ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

21፤ ከእርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ይላል እግዚአብሔር፥ በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ ከአፍህ ከዘርህም አፍ ከዘር ዘርህም አፍ አያልፍም፥ ይላል እግዚአብሔር።