ምዕራፍ 42።

1፤ እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፤ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፤ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል።

2፤ አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም።

3፤ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፤ በእውነት ፍርድን ያወጣል።

4፤ በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ይበራል እንጂ አይጠፋም፤ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ።

5፤ ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።

6፤7፤ እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለሁ፥ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፥ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ።

8፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም።

9፤ እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፤ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ።

10፤ ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርስዋም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፥ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፥ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፥ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ።

11፤ ምድረ በዳውና ከተሞቹ የቄዳርም ሰዎች የሚቀመጡባቸው መንደሮች ድምፃቸውን ያንሡ፤ በሴላ የሚኖሩ እልል ይበሉ፥ በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ።

12፤ ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፥ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ።

13፤ እግዚአብሔር እንደ ኃያል ይወጣል እንደ ሰልፈኛም ቅንዓትን ያስነሣል፤ ይጮኻል ድምፁንም ያሰማል በጠላቶቹም ላይ ይበረታል።

14፤ ከድሮ ዘመን ጀምሮ ዝም ብያለሁ፥ ዝም ብዬም ታግሻለሁ፤ አሁን ምጥ እንደ ያዛት ሴት እጮኻለሁ፤ አጠፋለሁ በአንድነትም እጨርሳለሁ።

15፤ ተራሮችንና ኮረብቶችን አፈርሳለሁ፥ ቡቃያዎቻቸውንም ሁሉ አደርቃለሁ፤ ወንዞችንም ደሴቶች አደርጋለሁ፥ ኵሬዎችንም አደርቃለሁ።

16፤ ዕውሮችንም በማያውቋት መንገድ አመጣቸዋለሁ፥ በማያውቋትም ጎዳና እመራቸዋለሁ፤ በፊታቸውም ጨለማውን ብርሃን አደርጋለሁ፥ ጠማማውንም አቀናለሁ። ይህን አደርግላቸዋለሁ፥ አልተዋቸውምም።

17፤ በተቀረጹትም ምስሎች የሚታመኑ፥ ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች። አምላኮቻችን ናችሁ የሚሉ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ ፈጽመውም ያፍራሉ።

18፤ እናንተ ደንቆሮች፥ ስሙ፤ እናንተም ዕውሮች፥ ታዩ ዘንድ ተመልከቱ።

19፤ ከባሪያዬ በቀር ዕውር ማን ነው? እንደምልከው መልእክተኛዬስ በቀር ደንቆሮ የሆነ ማን ነው? እንደ ፍጹሙ ወይስ እንደ እግዚአብሔር ባሪያ ዕውር የሆነ ማን ነው?

20፤ ብዙ ነገርን ታያላችሁ ነገር ግን አትጠባበቁትም፤ ጆሮአችሁም ተከፍተዋል፥ ነገር ግን አትሰሙም።

21፤ እግዚአብሔር ስለ ጽድቁ ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ ወደደ።

22፤ ይህ ግን የተበዘበዘና የተዘረፈ ሕዝብ ነው፤ ሁላቸው በዋሻ ውስጥ ተጠምደዋል በግዞት ቤትም ተሸሽገዋል፤ ብዝበዛ ሆነዋል የሚያድንም የለም፥ ምርኮም ሆነዋል፥ ማንም። መልሱ አይልም።

23፤ ከመካከላችሁ ይህን የሚያደምጥ፥ ለሚመጣውም ጊዜ የሚያደምጥና የሚሰማ ማን ነው?

24፤ ያዕቆብን ለማረኩ እስራኤልንም ለበዘበዙ ሰዎች የሰጠ ማን ነው? እኛ የበደልነው፥ እነርሱም በመንገዱ ይሄዱ ዘንድ ያልወደዱት ለሕጉም ያልታዘዙለት እግዚአብሔር እርሱ አይደለምን?

25፤ ስለዚህ የቍጣውን መዓትና የሰልፉን ጽናት አፈሰሰበት፤ በዙሪያም አነደደው እርሱ ግን አላወቀም፥ አቃጠለውም እርሱ ግን ልብ አላደረገም።