ምዕራፍ 23።

1፤ ስለ ጢሮስ የተነገረ ሸክም። የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ አልቅሱ፤ ፈርሶአልና ቤት የለም፥ መግባትም የለም፤ ከኪቲም አገር ጀምሮ ተገልጦላቸዋል።

2፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ በባሕርም የምትሻገሩ የሲዶና ነጋዴዎች ንግድ የሞሉባችሁ ሆይ፥ ጸጥ በሉ።

3፤ የሺሖር ዘርና የዓባይ ወንዝ መከር በብዙ ውኆች ላይ ገቢዋ ነበረ፤ እርስዋም የአሕዛብ መናገጃ ነበረች።

4፤ ሲዶና ሆይ፥ ባሕር፥ የባሕር ምሽግ። አላማጥሁም፥ አልወለድሁም፤ ጐበዛዝትንም አላሳደግሁም፥ ደናግልንም አላሳደግሁም ብሎ ተናግሮአልና እፈሪ።

5፤ ወሬዋ ወደ ግብጽ በደረሰ ጊዜ በጢሮስ ወሬ ምጥ ይይዛቸዋል።

6፤ ወደ ተርሴስ ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ አልቅሱ።

7፤ በቀድሞ ዘመን ተመሥርታ የነበረችው፥ በዚያም እንደ እንግዳ ሆና ትኖር ዘንድ እግሮችዋ ወደ ሩቅ ያፈለሱአት የደስታችሁ ከተማ ይህች ናትን?

8፤ አክሊል ባስጫነች ከተማ በጢሮስ ላይ ይህን የወሰነ ማን ነው? ነጋዴዎችዋ አለቆች ናቸው፥ በእርስዋም የሚሸጡና የሚለውጡ የምድር ክቡራን ናቸው።

9፤ የክብርን ሁሉ ትዕቢት ይሽር ዘንድ የምድርንም ክቡራን ሁሉ ያስንቅ ዘንድ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖታል።

10፤ የተርሴስ ልጅ ሆይ፥ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዓባይ ወንዝ በአገርሽ ላይ ጐርፈሽ እለፊ።

11፤ በባሕር ላይ እጁን ዘረጋ መንግሥታትንም አናወጠ፤ ምሽጎችዋንም ያጠፉ ዘንድ እግዚአብሔር ስለ ከነዓን አገር አዘዘ።

12፤ እርሱም። አንቺ የተበደልሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሥተሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፥ በዚያም ደግሞ አታርፊም አለ።

13፤ እነሆ፥ የከለዳውያን አገር! ይህ ሕዝብ ሆኖ አይገኝም፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል፤ ግንቦቻቸውን ሠሩ፥ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፥ ባድማም አደረጓት።

14፤ እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ።

15፤ በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዘመን ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች፤ ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል።

16፤ አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፥ መሰንቆ ያዢ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ ዘፈንሽንም አብዢ።

17፤ ከሰባ ዓመትም በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይጐበኛታል፥ ወደ ዋጋዋም ትምለሳለች፥ ደግሞም በምድር ፊት ላይ ከሆኑ ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር ትገለሙታለች።

18፤ ንግድዋና ዋጋዋ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋም በልተው ይጠግቡ ዘንድ ማለፊያም ልብስ ይለብሱ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩ ይሆናል እንጂ በዕቃ ቤትና በግምጃ ቤት ውስጥ አይከተትም።