ምዕራፍ 13።

1፤ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ያየው ስለ ባቢሎን የተንገረ ሸክም።

2፤ ምድረ በዳ በሆነ ተራራ ላይ ምልክትን አቁሙ፥ ድምፅንም ከፍ አድርጉባቸው፤ በአለቆችም ደጆች እንዲገቡ በእጅ ጥቀሱ።

3፤ ቍጣዬን ይፈጽሙ ዘንድ ቅዱሳኔን አዝዣለሁ፥ እኔ ኃያላኔንና በታላቅነቴ ደስ የሚላቸውን ጠርቻለሁ።

4፤ በተራሮች ላይ እንደ ታላቅ ሕዝብ ድምፅ የሆነ የብዙ ሰው ድምፅ አለ። የከተማቹት የአህዛብ መንግሥታት የውካታ ጫጫታ አለ። የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሠራዊትን ለሰልፍ አሰልፎአል።

5፤ እግዚአብሔርና የቍጣው የጦር ዕቃ ምድርን ሁሉ ያጠፉአት ዘንድ ከሩቅ አገር ከሰማይ ዳርቻ ይመጣሉ።

6፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፥ አልቅሱ፤ ሁሉን ከሚችል አምላክ ዘንድ እንደሚመጣ ጥፋት ይመጣል።

7፤ ስለዚህ እጅ ሁሉ ትዝላለች፥ የሰውም ሁሉ ልብ ይቀልጣል።

8፤ ይደነግጣሉ፤ ምጥና ሕማም ይይዛቸዋል፥ እንደምትወልድ ሴትም ያምጣሉ፤ አንዱም በሌላው ይደነቃል፥ ፊታቸውም የነበልባል ፊት ነው።

9፤ እነሆ፥ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ፥ ኃጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ ጨካኝ ሆኖ በመዓትና በጽኑ ቍጣ ተሞልቶ የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል።

10፤ የሰማይም ከዋክብትና ሠራዊቱ ብርሃናቸውን አይሰጡም፥ ፀሐይም በወጣች ጊዜ ትጨልማለች፥ ጨረቃም በብርሃኑ አያበራም።

11፤ ዓለሙን ስለ ክፋታቸው ክፉዎቹንም ስለ በደላቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኵራት አዋርዳለሁ።

12፤ የቀሩትም ከጥሩ ወርቅ ይልቅ የከበሩ ይሆናሉ፥ ሰውም ከኦፊር ወርቅ ይልቅ የከበረ ይሆናል።

13፤ ስለዚህ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር መዓት በጽኑ ቍጣ ቀንም ሰማያትን አነቃንቃለሁ፥ ምድርም ከስፍራዋ ትናወጣለች።

14፤ እንደ ተባረረም ሚዳቋ፥ ማንም እንደማይሰበስበው እንደ በግ መንጋ፥ ሰው ሁሉ ወደ ወገኑ ይመለሳል፥ ሁሉም ወደ አገሩ ይሸሻል።

15፤ የተገኘ ሁሉ የተወጋ ይሆናል፥ የተያዘም ሁሉ በሰይፍ ይወድቃል።

16፤ ሕፃናቶቻቸውም በፊታቸው ይጨፈጨፋሉ፥ ቤቶቻቸውም ይበዘበዛሉ፥ ሚስቶቻቸውም ይነወራሉ።

17፤ እነሆ፥ ብር የማይሹትን፥ ወርቅም የማያምራቸውን ሜዶናውያንን በላያቸው አስነሣለሁ።

18፤ ፍላጾቻቸውም ጎበዞችን ይጨፈጭፋሉ፥ የማኅፀንንም ፍሬ አይምሩም፥ ዓይኖቻቸውም ለሕፃናት አይራሩም።

19፤ እግዚአብሔርም ሰዶምንና ገሞራን ባፈረሰ ጊዜ እንደ ነበረው፥ የመንግሥታት ክብር የከለዳውያንም ትዕቢት ጌጥ ባቢሎን እንዲሁ ትሆናለች።

20፤ ለዘላለም የሚቀመጥባት አይገኝም፥ ከትውልድ እስከ ትውልድ ድረስ ሰው አይኖርባትም፤ ዓረባውያንም ድንኳንን በዚያ አይተክሉም፥ እረኞችም መንጎቻቸውን በዚያ አያሳርፉም።

21፤ በዚያም የምድረ በዳ አራዊት ያርፋሉ፥ ጕጕቶችም በቤቶቻቸው ይሞላሉ፤ ሰጎኖችም በዚያ ይኖራሉ፥ በዚያም አጋንንት ይዘፍናሉ።

22፤ ተኵላዎችም በግንቦቻቸው፥ ቀበሮችም በሚያማምሩ አዳራሾቻቸው ይጮኻሉ፤ ጊዜዋም ለመምጣት ቀርቦአል ቀንዋም አይዘገይም።