ምዕራፍ 8።

1፤ እግዚአብሔርም። ታላቅ ሰሌዳ ወስደህ። ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ በሰው ፊደል ጻፍበት።

2፤ የታመኑትን ሰዎች ካህኑን ኦርዮንና የበራክዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርግልኝ አለኝ።

3፤ ወደ ነቢይቱም ቀረብሁ፤ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች።

4፤ እግዚአብሔርም። ሕፃኑ አባቱንና እናቱን መጥራት ሳያውቅ የደማስቆን ሀብትና የሰማርያን ምርኮ በአሦር ንጉሥ ፊት ይወስዳልና ስሙን። ምርኮ ፈጠነ፥ ብዝበዛ ቸኰለ ብለህ ጥራው አለኝ።

5፤ እግዚአብሔርም ደግሞ ተናገረኝ እንዲህም አለኝ።

6፤ ይህ ሕዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሊሆምን ውኃ ጠልቶአልና፥ ረአሶንንና የሮሜልዩንም ልጅ ወዶአልና ስለዚህ፥

7፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውኃ፥ የአሦርን ንጉሥና ክብሩን ሁሉ፥ ያመጣባቸዋል፤ መስኖውንም ሁሉ ሞልቶ ይወጣል፥ በዳሩም ሁሉ ላይ ይፈስሳል፤

8፤ እየጐረፈም ወደ ይሁዳ ይገባል፤ እያጥለቀለቀም ያልፋል፥ እስከ አንገትም ይደርሳል፤ አማኑኤል ሆይ፥ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች።

9፤ አሕዛብ ሆይ፥ እወቁና ደንግጡ፤ እናንተም ምድራችሁ የራቀ ሁሉ፥ አድምጡ፤ ታጠቁም፥ ደንግጡ፤ ታጠቁ፤ ደንግጡ።

10፤ ተመካከሩ፥ ምክራችሁም ይፈታል፤ ቃሉን ተናገሩ፥ ቃሉም አይጸናም፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና።

11፤ እግዚአብሔርም በጽኑ እጅ እንዲህ ተናገረኝ፥ በዚህም ሕዝብ መንገድ አንዳልሄድ አስጠነቀቀኝ፥ እንዲህም አለኝ።

12፤ ይህ ሕዝብ። ዱለት ነው በሚሉት ሁሉ። ዱለት ነው አትበሉ፤ መፈራታቸውንም አትፍሩ፥ አትደንግጡ።

13፤ ነገር ግን የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርን ቀድሱት፤ የሚያስፈራችሁና የሚያስደነግጣችሁም እርሱ ይሁን።

14፤ እርሱም ለመቅደስ ይሆናል፤ ነገር ግን ለሁለቱ ለእስራኤል ቤቶች ለዕንቅፋት ድንጋይና ለማሰናከያ ዓለት፥ በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ለወጥመድና ለአሽክላ ይሆናል።

15፤ ብዙዎችም በእርሱ ይሰናከላሉ፥ ይወድቁማል፥ ይሰበሩማል፥ ይጠመዱማል፥ ይያዙማል።

16፤ ምስክሩን እሰር፤ በደቀ መዛሙርቶቼም መካከል ሕጉን አትም።

17፤ ከያዕቆብም ቤት ፊቱን የመለሰውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፥ እተማመንበትማለሁ።

18፤ እነሆ፥ እኔና እግዚአብሔር የሰጠኝ ልጆች ለእስራኤል በጽዮን ተራራ ከሚኖረው ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትና ተአምራት ነን።

19፤ እነርሱም። የሚጮኹትንና ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚናገሩትን መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ጠይቁ ባሉአችሁ ጊዜ፥ ሕዝቡ ከአምላኩ መጠየቅ አይገባውምን? ወይስ ለሕያዋን ሲሉ ሙታንን ይጠይቃሉን?

20፤ ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ! እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም።

21፤ እነርሱም ተጨንቀውና ተርበው ያልፋሉ፤ በተራቡም ጊዜ ተቈጥተው ንጉሣቸውንና አምላካቸውን ይረግማሉ፥ ወደ ላይም ይመለከታሉ፤

22፤ ወደ ምድርም ይመለከታሉ፥ እነሆም፥ መከራና ጨለማ የሚያስጨንቅም ጭጋግ አለ፤ ወደ ድቅድቅም ጨለማ ይሰደዳሉ።