ምዕራፍ 12።

1፤ ኤፍሬም በሐሰት፥ የእስራኤልም ቤት በተንኰል ከበበኝ፤ ይሁዳም ከታመነው ቅዱሱ ከእግዚአብሔር ጋር አይጸናም።

2፤ ኤፍሬም ነፋስን ይበላል፥ የምሥራቅንም ነፋስ ይከተላል፤ ሁልጊዜም ሐሰትንና ተንኰልን ያበዛል፤ ከአሦር ጋር ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፥ ወደ ግብጽም ዘይት ይወስዳሉ።

3፤ እግዚአብሔርም ደግሞ ከይሁዳ ጋር ክርክር አለው፥ ያዕቆብንም እንደ መንገዱ ይቀጣል፤ እንደ ሥራውም ይመልስለታል።

4፤ በማኅፀን ውስጥ ወንድሙን በተረከዙ ያዘው፥ በጕልማስነቱም ጊዜ ከአምላክ ጋር ታገለ፤

5፤ ከመልአኩም ጋር ታግሎ አሸነፈ፤ አልቅሶም ለመነው። በቤቴልም አገኘው፥ በዚያም ከእኛ ጋር ተነጋገረ።

6፤ እርሱም የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው፤ የመታሰቢያው ስም እግዚአብሔር ነው።

7፤ ስለዚህ ወደ አምላክህ ተመለስ፤ ምሕረትንና ፍርድን ጠብቅ፥ ዘወትርም በአምላክህ ታመን።

8፤ ከከነዓን ወገን ነው፤ በእጁ የተንኰል ሚዛን አለ፥ ሽንገላንም ይወድዳል።

9፤ ኤፍሬምም። ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ፥ ሀብትንም አግኝቻለሁ፥ በድካሜም ሁሉ ኃጢአት የሚሆን በደል አይገኝብኝም አለ።

10፤ እኔም ከግብጽ ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ እንደ ዓመት በዓል ቀን እንደ ገና በድንኳን እንድትኖር አደርግሃለሁ።

11፤ ለነቢያትም ተናግሬአለሁ፥ ራእይንም አብዝቻለሁ፤ በነቢያትም እጅ ምሳሌዎችን አውጥቻለሁ።

12፤ ኃጢአት በገለዓድ አለ፤ ፈጽመው ከንቱ ናቸው፤ ወይፈኖች በጌልገላ ይሠዋሉ፥ መሠዊያዎቻቸውም በእርሻ ትልም ላይ የድንጋይ ክምር ይሆናሉ።

13፤ ያዕቆብ ወደ ሶርያ አገር ሸሸ፥ እስራኤልም ስለ ሚስት አገለገለ፥ ስለ ሚስትም ጠባቂ ነበረ።

14፤ እግዚአብሔርም በነቢይ እጅ እስራኤልን ከግብጽ አወጣ፥ በነቢይም እጅ ጠበቀው።

15፤ ኤፍሬም አስመርሮ አስቈጣው፤ ስለዚህ ደሙ በላዩ ላይ ነው፤ ጌታውም ስድቡን በራሱ ላይ ይመልሳል።