ምዕራፍ 5።

1፤ ካህናት ሆይ፥ ይህን ስሙ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ አድምጡ፤ የንጉሥ ቤት ሆይ፥ ልብ አድርጉ፤ በምጽጳ ላይ ወጥመድ፥ በታቦርም ላይ የተዘረጋ አሽክላ ሆናችኋልና ፍርድ በእናንተ ላይ ነው።

2፤ ዓመፀኞችም እርድ አብዝተዋል፤ እኔ ግን እነዚያን ሁሉ እዘልፋለሁ።

3፤ ኤፍሬምን አውቀዋለሁ፥ እስራኤልም ከእኔ አልተሰወረም፤ ኤፍሬም ሆይ፥ ዛሬ አመንዝረሃል፥ እስራኤልም ረክሶአል።

4፤ ወደ አምላካቸው ይመለሱ ዘንድ ሥራቸውን አላቀኑም፤ የግልሙትና መንፈስ በውስጣቸው አለና፤ እግዚአብሔርንም አላውቁምና።

5፤ የእስራኤልም ትዕቢት በፊቱ ይመሰክራል፤ ስለዚህ እስራኤልና ኤፍሬም በኃጢአታቸው ይሰናከላሉ፤ ይሁዳም ደግሞ ከእነሱ ጋር ይሰናከላል።

6፤ እግዚአብሔርንም ለመሻት በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ነድተው ይሄዳሉ፤ ነገር ግን እርሱ ከእነርሱም ተመልሶአልና አያገኙትም።

7፤ ዲቃሎችን ልጆች ወልደዋልና እግዚአብሔርን ወንጅለዋል፤ አሁንም አንድ ወር እነርሱንና ርስታቸውን ይበላቸዋል።

8፤ በጊብዓ መለከትን፥ በራማ እንቢልታን ንፉና። ብንያም ሆይ፥ ከአንተ በኋላ እያላችሁ በቤትአዌን ላይ እሪ በሉ።

9፤ ኤፍሬም በዘለፋ ቀን የፈረሰ ይሆናል። በእስራኤል ነገዶች ዘንድ በእርግጥ የሚሆነውን ነገር ገልጫለሁ።

10፤ የይሁዳ አለቆች ድምበርን እንደሚነቅሉ ሆነዋል፤ እኔም መዓቴን እንደ ውኃ አፈስስባቸዋለሁ።

11፤ ኤፍሬም ከትእዛዝ በኋላ መሄድን ወድዶአልና የተገፋና በፍርድ የተጐዳ ሆኖአል።

12፤ እኔም ለኤፍሬም እንደ ብል፥ ለይሁዳም ቤት እንደ ነቀዝ ሆኜአለሁ።

13፤ ኤፍሬምም ደዌውን፥ ይሁዳም ቍስሉን ባየ ጊዜ ኤፍሬም ወደ አሦር ሄደ ወደ ንጉሡም ወደ ኢያሪም መልእክተኛን ላከ፤ እርሱ ግን ይፈውሳችሁ ዘንድ፥ ከቊስላችሁም ያድናችሁ ዘንድ አልቻለም።

14፤ እኔም ለኤፍሬም እንደ አንበሳ፥ ለይሁዳም ቤት እንደ አንበሳ ደቦል እሆናለሁና፤ እኔም ነጥቄ እሄዳለሁ እወስድማለሁ፥ የሚያድንም አይገኝም።

15፤ በደላቸውንም እስኪያውቁ ድረስ፥ ፊቴንም እስኪሹ ድረስ ሄጄ ወደ ስፍራዬ እመለሳለሁ፤ በመከራቸው ጊዜ እጅግ አድርገው ፊቴን ይፈልጋሉ።