ምዕራፍ 2።

1፤ በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ የሚናገረኝንም፥ ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ።

2፤ እግዚአብሔርም መለሰልኝ እንዲህም አለ። አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ፥ በጽላትም ላይ ግለጠው።

3፤ ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም፤ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱ አይዘገይም።

4፤ እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል።

5፤ እርሱ አታላይና ኵሩ ሰው ነው፤ በስፍራው ዐርፎ አይቀመጥም፤ ስስቱን እንደ ሲኦል ያሰፋል፥ እርሱም እንደ ሞት አይጠግብም፤ አሕዛብንም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበስባል፥ ወገኖቹንም ሁሉ ወደ እርሱ ያከማቻል።

6፤ እነዚህ ሁሉ። ለእርሱ ያልሆነውን ወደ እርሱ ለሚሰበስብ መያዣውንም ለራሱ የሚያበዛ ወዮለት! እስከ መቼ ነው? እያሉ ምሳሌ አይመስሉበትምን?

7፤ ተረትም አይተርቱበትምን? የሚነክሱህ ድንገት አይነሡብህምን? የሚያስጨንቁህም ይነቃሉ፤ ለእነርሱም ብዝበዛ ትሆናለህ።

8፤ የሰውን ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ አንተ ብዙዎችን አሕዛብን በዝብዘሃልና ከአሕዛብ የቀሩት ሁሉ ይበዘብዙሃል።

9፤ ከክፉ እንዲድን ጐጆውን በከፍታ ላይ ያደርግ ዘንድ ለቤቱ ክፉ ትርፍን ለሚሰበስብ ወዮለት!

10፤ ብዙ አሕዛብን አጥፍተሃልና ለቤትህ እፍረትን መክረሃል፥ በነፍስህም ላይ ኃጢአትን አድርገሃል።

11፤ ድንጋይም ከግንብ ውስጥ ይጮኻል፥ እንጨትም ከውቅር ውስጥ ይመልስለታል።

12፤ ከተማን በደም ለሚሠራ፥ ከተማንም በኃጢአት ለሚመሠርት ወዮለት!

13፤ እነሆ፥ አሕዛብ ስለ እሳት እንዲሠሩ፥ ወገኖችም ስለ ከንቱነት እንዲደክሙ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ አይደለምን?

14፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለችና።

15፤ ኀፍረተ ሥጋውን ለማየት ባልንጀራውን ለሚያጠጣ፥ ክፉንም ለሚጨምርበት፥ ለሚያሰክረውም ወዮለት!

16፤ በክብር ፋንታ እፍረት ሞልቶብሃል፤ አንተ ደግሞ ጠጥተህ ተንገድገድ፤ የእግዚአብሔር የቀኙ ጽዋ ይመለስብሃል፥ እፍረትም በክብርህ ላይ ይሆናል።

17፤ የሰውንም ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ በሊባኖስ ላይ የሠራኸው ግፍ ይከድንሃል፤ የአራዊትም አደጋ ያስፈራራሃል።

18፤ የተቀረጸውን ምስል ሠሪው የቀረጸው ለምን ጥቅም ነው? ዲዳንም ጣዖት ይሠራ ዘንድ ሠሪው የታመነበቱ፥ ሐሰትን የሚያስተምር ቀልጦ የተሠራ ምን ይጠቅማል?

19፤ እንጨቱን። ንቃ፥ ዲዳውንም ድንጋይ። ተነሣ ለሚለው ወዮለት! በውኑ ይህ ያስተምራልን? እነሆ፥ በወርቅና በብር ተለብጦአል፥ ምንም እስትንፋስ የለበትም።

20፤ እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ ምድርም ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል።