ምዕራፍ 19።

1፤ ሁለቱም መላእክት በመሸ ጊዜ ወደ ሰዶም ገቡ፤ ሎጥም በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር። ሎጥም ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ተነሣ፤ ፊቱንም ደፍቶ ወደ ምድር ሰገደ፥ አላቸውም።

2፤ ጌቶቼ ሆይ፥ ወደ ባሪያችሁ ቤት አቅኑ፥ ከዚያም እደሩ፥ እግራችሁንም ታጠቡ፤ ነገ ማልዳችሁም መንገዳችሁን ትሄዳላችሁ። እነርሱም። በአደባባዩ እናድራለን እንጂ፥ አይሆንም አሉት።

3፤ እጅግም ዘበዘባቸው፤ ወደ እርሱም አቀኑ፥ ወደ ቤቱም ገቡ፤ ማዕድ አቀረበላቸው፥ ቂጣንም ጋገረ እነርሱም በሉ።

4፤ ገናም ሳይተኙ የዚያች ከተማ የሰዶም ሰዎች፥ ከብላቴናው ጀምሮ እስከ ሽማግሌው ድረስ በየስፍራው ያለው ሕዝብ ሁሉ፥ ቤቱን ከበቡት።

5፤ ሎጥንም ጠርተው እንዲህ አሉት። በዚህ ሌሊት ወደ ቤትህ የገቡት ሰዎች ወዴት ናቸው? እናውቃቸው ዘንድ ወደ እኛ አውጣቸው።

6፤ ሎጥም ወደ እነርሱ ወደ ደጅ ወጣ መዝጊያውንም በኋላው ዘጋው፤

7፤ እንዲህም አለ። ወንድሞቼ ሆይ፥ ይህን ክፉ ነገር አታድርጉ፤

8፤ እነሆ፥ ወንድን ያላወቁ ሁለት ሴቶች ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ላውጣላችሁ፥ እንደ ወደዳችሁም አድርጓቸው፤ በእነዚህ ሰዎች ብቻ ምንም አታድርጉ፥ እነርሱ በጣራዬ ጥላ ሥር ገብተዋልና።

9፤ እነርሱም። ወዲያ ሂድ አሉት። ደግሞም እንዲህ አሉ። ይህ ሰው በእንግድነት ለመኖር መጣ፥ ፍርዱንም ይፈርድ ዘንድ ይፈልጋል፤ አሁን በአንተ ከእነርሱ ይልቅ ክፉ እናደርግብሃለን። ሎጥንም እጅግ ተጋፉት፥ የደጁንም መዝጊያ ለመስበር ቀረቡ።

10፤ ሁለቱም ሰዎች እጃቸውን ዘርግተው ሎጥን ወደ እነርሱ ዘንድ ወደ ቤት አገቡት መዝጊያውንም ዘጉት።

11፤ በቤቱ ደጃፍ የነበሩትንም ሰዎች ከታናሻቸው ጀምሮ እስከ ታለቃቸው ድረስ አሳወሩአቸው፤ ደጃፉንም ለማግኘት ሲፈልጉ ደከሙ።

12፤ ሁለቱም ሰዎች ሎጥን አሉት። ከዚህ ሌላ ማን አለህ? አማችም ቢሆን ወንድ ልጅም ቢሆን ወይም ሴት ልጅ ብትሆን በከተማይቱ ያለህን ሁሉ ከዚህ ስፍራ አስወጣቸው፤

13፤ እኛ ይህን ስፍራ እናጠፋለንና፥ ጩኸታቸው በእግዚአብሔር ፊት ትልቅ ሆኖአልና፤ እናጠፋውም ዘንድ እግዚአብሔር ሰድዶናል።

14፤ ሎጥም ወጣ፥ ልጆቹን ለሚያገቡት ለአማቾቹም ነገራቸው፥ አላቸውም። ተነሡ፤ ከዚህ ስፍራ ውጡ፤ እግዚአብሔር ይህችን ከተማ ያጠፋልና። ለአማቾቹ ግን የሚያፌዝባቸው መሰላቸው።

15፤ ጎህም በቀደደ ጊዜ መላእክት ሎጥን። ተነሣ፥ ሚስትህንና ከዚህ ያሉትን ሁለቱን ሴቶች ልጆችህን ውሰድ፤ በከተማይቱ ኃጢአት እንዳትጠፋ እያሉ ያስቸኵሉት ነበር።

16፤ እርሱም በዘገየ ጊዜ እግዚአብሔር ስላዘነለት እነዚያ ሰዎች የእርሱን እጅ የሚስቱንም እጅ የሁለቱን የሴቶች ልጆቹንም እጅ ይዘው አወጡትና በከተማይቱ ውጭ አስቀመጡት።

17፤ ወደ ሜዳም ካወጡአቸው በኋላ እንዲህ አለው። ራስህን አድን፤ ወደ ኋላህ አትይ፥ በዚህም ዙሪያ ሁሉ አትቁም እንዳትጠፋም ወደ ተራራው ሸሽተህ አምልጥ።

18፤ ሎጥም፤ አላቸው። ጌቶቼ ሆይ፥ እንዲህስ አይሁን፤

19፤ እነሆ ባሪያህ በፊትህ ሞገስን አግኝቶአል፥ ነፍሴን ለማዳን ያደረግህልኝን ምሕረትህንም አብዝተሃል፤ ክፉ እንዳያገኘኝና እንዳልሞት ወደ ተራራ ሸሽቼ አመልጥ ዘንድ አልችልም፤

20፤ እነሆ ይህች ከተማ ወደ እርስዋ ሸሽቶ ለማምለጥ ቅርብ ናት፥ እርስዋም ትንሽ ናት፤ ነፍሴን ለማዳን ወደ እርስዋ ሸሽቼ ላምልጥ፤ እርስዋ ትንሽ ከተማ አይደለችምን?

21፤ እርሱም አለው። የተናገርሃትን ከተማ እንዳላጠፋት እነሆ በዚህ ነገር የለመንኸኝን ተቀብዬሃለሁ፤

22፤ በቶሎ ወደዚያ ሸሽትህ አምልጥ፤ ወደዚያ እስክትደርስ ድረስ ምንም አደርግ ዘንድ አልችልምና። ስለዚህም የዚያች ከተማ ስም ዞዓር ተባለ።

23፤ ሎጥ ወደ ዞዓር በገባ ጊዜ ፀሐይ በምድር ላይ ወጣች።

24፤ እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤

25፤ እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ።

26፤ የሎጥም ሚስት ወደ ኋላዋ ተመለከተች፥ የጨው ሐውልትም ሆነች።

27፤ አብርሃምም በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ወደ ነበረበት ስፍራ ለመሄድ ማልዶ ተነሣ፤

28፤ ወደ ሰዶምና ወደ ገሞራ በዚያች አገር ወዳለውም ምድር ሁሉ ተመለከተ፤ እነሆም የአገሪቱ ጢስ እንደ እቶን ጢስ ሲነሣ አየ።

29፤ እግዚአብሔርም እነዚያን የአገር ከተሞች ባጠፋ ጊዜ አብርሃምን አሰበው፤ ሎጥ ተቀምጦበት የነበረውንም ከተማ ባጠፋ ጊዜ ከዚያ ጥፋት መካከል ሎጥን አወጣው።

30፤ ሎጥም ከዞዓር ወጣ፤ በዞዓር ይቀመጥ ዘንድ ስለ ፈራም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር በተራራ ተቀመጠ፤ በዋሻም ከሁለቱ ሴቶች ልጆቹ ጋር ተቀመጠ።

31፤ ታላቂቱም ታናሺቱን አለቻት። አባታችን ሸመገለ፥ በምድርም ሁሉ እንዳለው ልማድ ሊገናኘን የሚችል ሰው ከምድር ላይ የለም፤

32፤ ነዪ አባታቻንንም የወይን ጠጅ እናጠጣውና ከእርሱ ጋር እንተኛ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር።

33፤ በዚያችም ሌሊት አባታቸውን የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ታላቂቱም ገባች፥ ከአባትዋም ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም።

34፤ በነጋውም ታላቂቱ ታናሺቱን አለቻት። እነሆ ትናንት ከአባቴ ጋር ተኛሁ፤ ዛሬ ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ እናጠጣው አንቺም ግቢና ከእርሱ ጋር ተኚ፥ ከአባታችንም ዘር እናስቀር።

35፤ አባታቸውንም በዚያች ሌሊት ደግሞ የወይን ጠጅ አጠጡት፤ ታናሺቱም ገብታ ከእርሱ ጋር ተኛች፤ እርሱም ስትተኛና ስትነሣ አላወቀም።

36፤ የሎጥም ሁለቱ ሴቶች ልጆች ከአባታቸው ፀነሱ።

37፤ ታላቂቱም ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም ሞዓብ ብላ ጠራችው፤ እርሱም እስከ ዛሬ የሞዓባውያን አባት ነው።

38፤ ታናሺቱም ደግሞ ወንድ ልጅ ወለደች ስሙንም። የወገኔ ልጅ ስትል አሞን ብላ ጠራችው፤ እርሱም እስከ ዛሬ የአሞናውያን አባት ነው።