ምዕራፍ 7።

1፤ እግዚአብሔርም ኖኅን አለው። አንተ ቤተሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፤ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና።

2፤3፤ ከንጹሕ እንስሳ ሁሉ ሰባት ሰባት ተባትና እንስት፥ ንጹሕ ካልሆነ እንስሳም ሁለት ሁለት ተባትና እንስት፥ ከሰማይ ወፍ ደግሞ ሰባት ሰባት ተባትና እንስት እያደረግህ በምድር ላይ ለዘር ይቀር ዘንድ ለአንተ ትወስዳለህ።

4፤ ከሰባት ቀን በኋላ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ አዘንባለሁና፤ የፈጠርሁትንም ፍጥረት ሁሉ ከምድር ላይ አጠፉለሁና።

5፤ ኖኅም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ አደረገ።

6፤ ኖኅም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በሆነ ጊዜ የስድስት መቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ።

7፤ ኖኅም ስለ ጥፋት ውኃ ልጆቹንና ሚስቱን የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወደ መርከብ ገባ።

8፤ ከንጹሕ እንስሳ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰውም ሁሉ፥

9፤ እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው፥ ሁለት ሁለት ተባትና እንስት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ።

10፤ ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሆነ።

11፤ በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በአሥራ ሰባተኛው ዕለት፥ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፥ የሰማይም መስኮቶች ተከፈቱ፤

12፤ ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ።

13፤ በዚያውም ቀን ኖኅ ወደ መርከብ ገባ፥ የኖኅ ልጆችም ሴም ካም ያፌትና የኖኅ ሚስት ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከርሱ ጋር ገቡ።

14፤ እነርሱ፥ አራዊትም ሁሉ በየወገናቸው፥ እንስሳትም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾችም ሁሉ በየወገናቸው፥ ወፎችም ሁሉ በየወገናቸው፥ የሚበሩ ወፎችም ሁሉ፥

15፤ ሥጋ ያላቸው ሕያዋን ሁሉ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ።

16፤ ሥጋ ካለው ሁሉ የገቡትም ተባትና እንስት እግዚአብሔር እንዳዘዘው ገቡ፤ እግዚአብሔርም በስተ ኋላው ዘጋበት።

17፤ የጥፋትም ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀን ነበረ፤ ውኃውም በዛ መርከቢቱንም አነሣ፥ ከምድርም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለች።

18፤ ውኃውም አሸነፈ፥ በምድር ላይም እጅግ በዛ፤ መርከቢቱም በውኃ ላይ ሄደች።

19፤ ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ፤ ከሰማይም በታች ያሉ ታላላቆች ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ።

20፤ ውኃው ወደ ላይ አሥራ አምስት ክንድ ከፍ ከፍ አለ፤ ተራሮችም ተሸፈኑ።

21፤ በምድር ላይ ሥጋ ያለው የሚንቀሳቀሰው ሁሉ፥ ወፉም፥ እንስሳውም፥ አራዊቱም፥ በምድር ላይ የሚርመሰመሰው ተንቀሳቃሹም ሁሉ፥ ሰውም ሁሉ ጠፋ።

22፤ በየብስ የነበረው በአፍንጫው የሕይወት ነፍስ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሞተ።

23፤ በምድር ላይ የነበረውም ሁሉ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ፥ እስከሚርመሰመሰውም ሁሉ ድረስ፥ እስከ ሰማይ ወፍ ድረስ ተደመሰሰ፤ ከምድርም ተደመሰሱ። ኖኅም አብረውት በመርከብ ከነበሩት ጋር ብቻውን ቀረ።

24፤ ውኃውም መቶ አምሳ ቀን በምድር ላይ አሸነፈ።