ምዕራፍ 5።

1፤ ነቢያቱም ሐጌና የአዶ ልጅ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩ አይሁድ በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው።

2፤ በዚያን ጊዜ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል የኢዮሴዴቅም ልጅ ኢያሱ ተነሥተው በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመሩ፤ የሚያግዙአቸውም የእግዚአብሔር ነቢያት ከእነርሱ ጋር ነበሩ።

3፤ በዚያም ዘመን በወንዝ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ ሰተርቡዝናይ፥ ተባባሪዎቻቸውም ወደ እነርሱ መጥተው። ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንኑም ቅጥር ታድሱ ዘንድ ያዘዛችሁ ማን ነው? አሉአቸው።

4፤ ደግሞም። ይህንስ ሥራ የሚሠሩት ሰዎች ስም ማን ነው? ብለው ጠየቁአቸው።

5፤ የአምላካቸው ዓይን ግን በአይሁድ ሽማግሌዎች ላይ ነበረ፥ ይህም ነገር ወደ ዳርዮስ እስኪደርስ ድረስ፥ መልሱም በደብዳቤ እስኪመጣ ድረስ አልከለከሉአቸውም።

6፤ በወንዙ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ ተባባሪዎቹም በወንዙ ማዶ የነበሩት አፈርስካውያን ወደ ንጉሡ ወደ ዳርዮስ የላኩት የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነበረ።

7፤ እንዲህም የሚል ደብዳቤ ላኩለት። ለንጉሡ ለዳርዮስ ሙሉ ሰላም ይሁን፤

8፤ ወደ ይሁዳ አገር ወደ ታላቁም አምላክ ቤት እንደ ሄድን ንጉሡ ይወቅ፤ እርሱም በትልቅ ድንጋይ ተሠራ፥ በቅጥሩም ውስጥ እንጨት ተደረገ፥ ያም ሥራ በትጋት ይሠራል፥ በእጃቸውም ይከናወናል።

9፤ እነዚያንም ሽማግሌዎች። ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንስ ቅጥር ታድሱ ዘንድ ያዘዛችሁ ማን ነው? ብለን ጠየቅናቸው።

10፤ ደግሞም እናስታውቅህ ዘንድ፥ በእነርሱም ያሉትን ሹሞች ስም እንጽፍልህ ዘንድ ስማቸውን ጠየቅን።

11፤ እንደዚህም ብለው መለሱልን። እኛ የሰማይና የምድር አምላክ ባሪያዎች ነን፥ ከብዙም ዘመን ጀምሮ ተሠርቶ የነበረውን፥ ታላቁም የእስራኤል ንጉሥ ሠርቶ የፈጸመውን ቤት እንሠራለን።

12፤ አባቶቻችንም የሰማይን አምላክ ካስቈጡ በኋላ በከለዳዊው በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ እርሱም ይህን ቤት አፈረሰ፥ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ።

13፤ ነገር ግን በባቢሎን ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ አዘዘ።

14፤ ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ የወሰደውን፥ ወደ ባቢሎንም መቅደስ ያፈለሰውን የእግዚአብሔርን ቤት የወርቅንና የብርን ዕቃ ንጉሡ ቂሮስ ከባቢሎን መቅደስ አውጥቶ ሰሳብሳር ለተባለው ለሹሙ ሰጠውና።

15፤ ይህን ዕቃ ይዘህ ሂድ፥ በኢየሩሳሌምም ባለው መቅደስ አኑረው፤ የእግዚአብሔርም ቤት በስፍራው ይሠራ አለው።

16፤ በዚያ ጊዜም ይህ ሰሳብሳር መጣ፥ በኢየሩሳሌምም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሠረተ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እየተሠራ አልተጨረሰም።

17፤ አሁንም ይህ ነገር በንጉሡ ዓይን መልካም ቢሆን ይህ የእግዚአብሔር ቤት በኢየሩሳሌም ይሠራ ዘንድ ከንጉሡ ከቂሮስ ታዝዞ እንደ ሆነ በባቢሎን ባለው በንጉሡ ቤተ መዛግብት ይመርመር፤ ስለዚህም ነገር ንጉሡ ፈቃዱን ይላክልን።