ምዕራፍ 47።

1፤ ወደ መቅደሱም መዝጊያ መለሰኝ፤ እነሆም፥ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ ከቀኝ ወገን በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር።

2፤ በሰሜኑም በር በኩል አወጣኝ፤ በስተ ውጭ ባለው መንገድ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከት በስተ ውጭ ወዳለው በር አዞረኝ፤ እነሆም፥ ውኃው በቀኙ ወገን ይፈስስ ነበር።

3፤ ሰውዬውም ገመዱን በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ አንድ ሺህም ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃም እስከ ቍርጭምጭሚት ደረሰ።

4፤ ደግሞ አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ጕልበት ደረሰ። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሻገረኝ፥ ውኃውም እስከ ወገብ ደረሰ።

5፤ ደግሞ አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ።

6፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ አይተሃልን? አለኝ። አመጣኝም፥ ወደ ወንዙም ዳር መለሰኝ።

7፤ በተመለስሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ።

8፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። ይህ ውኃ ወደ ምሥራቅ ምድር ይወጣል ወደ ዓረባም ይወርዳል ወደ ባሕሩም ይገባል፤ ወደ ባሕሩም ወደ ረከሰው ውኃ በገባ ጊዜ ውኃው ይፈወሳል።

9፤ ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ ወንዙ በመጣበት ስፍራ ሁሉ በሕይወት ይኖራል፤ ይህም ውኃ በዚያ ስለ ደረሰ ዓሣዎች እጅግ ይበዛሉ፤ የባሕሩም ውኃ ይፈወሳል፥ ወንዙም በሚመጣበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል።

10፤ አጥማጆችም በዚያ ይቆማሉ፤ ከዓይንጋዲ ጀምሮ እስከ ዓይንኤግላይም ድረስ መረብ መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣዎችም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣዎች በየወገናቸው እጅግ ይበዛሉ።

11፤ እረግረጉና እቋሪው ውኃ ግን ጨው እንደ ሆነ ይኖራል እንጂ አይፈወስም።

12፤ በወንዙም አጠገብ በዳሩ ላይ በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉም አይረግፍም ፍሬውም አይጐድልም፤ ውኃውም ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኵር ያገኛል፤ ፍሬውም ለመብል ቅጠሉም ለመድኃኒት ይሆናል።

13፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ርስት አድርጋችሁ ለአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን የምትከፍሉበት ድንበር ይህ ነው። ለዮሴፍ ሁለት እድል ፈንታ ይሆናል።

14፤ ለአባቶቻችሁ እሰጣቸው ዘንድ ምዬ ነበርና እናንተ እኩል አድርጋችሁ ተካፈሉት ይህችም ምድር ርስት ትሆናችኋለች።

15፤ የምድሪቱም ድንበር ይህ ነው። በሰሜኑ ወገን ከታላቁ ባሕር ጀምሮ በሔትሎን መንገድ ወደ ጽዳድ መግቢያ፤

16፤ ሐማት፥ ቤሮታ፥ በደማስቆ ድንበርና በሐማት ድንበር መካከል ያለው ሲብራይም፥ በሐውራን ድንበር አጠገብ ያለው ሐጸርሃቲኮን።

17፤ ድንበሩ ከባሕሩ በደማስቆ ድንበር ላይ ያለው ሐጸርዔናን ይሆናል፥ በሰሜንም በኩል የሐማት ድንበር አለ። የሰሜኑ ድንበር ይህ ነው።

18፤ የምሥራቁም ድንበር በሐውራን በደማስቆና በገለዓድ በእስራኤልም ምድር መካከል ዮርዳኖስ ይሆናል። ከሰሜኑ ድንበር ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ባሕር እስከ ታማር ድረስ የምሥራቁ ድንበር ይህ ነው።

19፤ የደቡቡም ድንበር ከታማር ጀምሮ እስከ ሜርባ ቃዴስ ውኃ እስከ ግብጽ ወንዝ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። የደቡቡ ድንበር ይህ ነው።

20፤ የምዕራቡም ድንበር ከደቡቡ ድንበር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ታላቁ ባሕር ይሆናል። የምዕራቡ ድንበር ይህ ነው።

21፤ እንዲሁ ይህችን ምድር እንደ እስራኤል ነገዶች መጠን ለእናንተ ትካፈላላችሁ።

22፤ ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆችን ለሚወልዱ መጻተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ የአገር ልጆች ይሆኑላችኋል፥ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ።

23፤ መጻተኛውም በማናቸውም ነገድ መካከል ቢቀመጥ በዚያ ርስቱን ትሰጡታላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።