ምዕራፍ 7።

1፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

2፤ አንተ የሰው ልጅ ሆይ፥ ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤል ምድር እንዲህ ይላል። ፍጻሜ፥ በምድሪቱ በአራቱ ማዕዘን ላይ ፍጻሜ ደርሶአል።

3፤ አሁን ፍጻሜ በአንቺ ላይ ነው፥ ቍጣዬንም እሰድድብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ።

4፤ ዓይኔም አይራራልሽም እኔም አላዝንም፤ መንገድሽንም አመጣብሻለሁ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

5፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ክፉ ነገር፥ አንድ ክፉ ነገር፥ እነሆ፥ ይመጣል።

6፤ ፍጻሜ መጥቶአል፥ ፍጻሜ መጥቶአል፥ ነቅቶብሻል፤ እነሆ፥ ደርሶአል።

7፤ በምድር የምትቀመጥ ሆይ፥ ተራህ ደርሶአል፥ ጊዜ መጥቶአል፥ ቀን ቀርቦአል፤ የሽብር ቀን ነው እንጂ በተራራ ላይ ያለ እልልታ አይደለም።

8፤ አሁን በቅርብ መዓቴን አፈስስብሻለሁ፥ ቍጣዬንም እፈጽምብሻለሁ፥ እንደ መንገድሽም መጠን እፈርድብሻለሁ፥ ጕስቍልናሽንም ሁሉ አመጣብሻለሁ።

9፤ ዓይኔም አይራራም እኔም አላዝንም፤ እንደ መንገድሽም መጠን አመጣብሻለሁ፥ ርኵሰትሽም በመካከልሽ ይሆናል፥ እኔም እግዚአብሔር የምቀሥፍ እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

10፤ እነሆ ቀኑ፥ እነሆ፥ መጥቶአል፤ ተራህ ወጥቶአል፤ ብትር አብቦአል፥ ትዕቢትም አጅብጅፎአል።

11፤ ግፍ ወደ ክፋት ብትር ተነስቶአል፤ ከእነርሱና ከብዛታቸው ከሀብታቸውም ምንም አይቀርም፥ የሚያለቅስላቸውም የለም።

12፤ ጊዜው መጥቶአል፥ ቀኑ ቀርቦአል፤ መዓት በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና የሚገዛ ደስ አይበለው የሚሸጥም አያልቅስ።

13፤ የሚሸጥ ወደሸጠው ነገር አይመለስም፥ ሰውም በነፍሱ ኃጢአት አይጸናም።

14፤ መለከቱን ነፍተዋል ሁሉንም አዘጋጅተዋል፤ ነገር ግን መዓቴ በብዙዎች ሁሉ ላይ ነውና ወደ ሰልፍ የሚሄድ የለም።

15፤ ሰይፍ በውጭ ቸነፈርና ራብ በውስጥ አለ፤ በሜዳ ያለው በሰይፍ ይሞታል፥ በከተማም ያለውን ቸነፈርና ራብ ይፈጁታል።

16፤ ከእነርሱም የሚሸሹ ይድናሉ በተራራም ላይ ይሆናሉ፤ እኔም በኃጢአታቸው ሁሉን እገድላለሁ።

17፤ እጅ ሁሉ ትደክማለች ጕልበትም ሁሉ እንደ ውኃ ትቀልጣለች።

18፤ ማቅም ይለብሳሉ ድንጋጤም ይሸፍናቸዋል፤ በፊትም ሁሉ ላይ እፈረት ይሆናል፥ ራሳቸውንም ሁሉ ይነጩታል።

19፤ ብራቸውን በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ ወርቃቸውም እንደ ጕድፍ ይሆናል፤ በእግዚአብሔር መዓት ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ያድናቸው ዘንድ አይችልም። እርሱ የኃጢአታቸው ዕንቅፋት ሆኖአልና ሰውነታቸውን አያጠግቡም ሆዳቸውንም አይሞሉም።

20፤ የክብሩንም ጌጥ ወደ ትዕቢት ለወጡ፥ የርኵስነታቸውንም ምስሎች አደረጉባት፤ ስለዚህ እኔ በእነርሱ ዘንድ ርኩስ አድርጌአታለሁ።

21፤ በባዕድም እጅ ለንጥቂያ፥ በምድር ኃጢአተኞችም እጅ ለብዝበዛ አሳልፌ እሰጣታለሁ፤ እነርሱም ያረክሱአታል።

22፤ ፊቴን ከእነርሱ ዘንድ እመልሳለሁ፥ ምሥጢሬንም ያረክሳሉ፤ ወንበዴዎችም ይገቡባታል ያረክሱአትማል።

23፤ ምድር ደም ባመጣው በደል፥ ከተማም በግፍ ተሞልታለችና ሰንሰለት ሥራ።

24፤ ከአሕዛብ ዘንድ ከሁሉ የሚከፉትን አመጣለሁ ቤቶቻቸውንም ይወርሳሉ፤ የኃያላንንም ትዕቢት አጠፋለሁ፥ መቅደሶቻቸውም ይረክሳሉ።

25፤ ጥፋት መጥቶአል፤ ሰላምም ይሻሉ እርሱም አይገኝም።

26፤ ድንጋጤ በድንጋጤ ላይ ይመጣል፥ ወሬም ወሬውን ይከተላል፥ ከነቢዩም ዘንድ ራዕይን ይሻሉ፤ ከካህኑም ዘንድ ትምህርት፥ ከሽማግሌዎችም ዘንድ ምክር ይጠፋል።

27፤ ንጉሡም ያለቅሳል፥ አለቃም ውርደትን ይለብሳል፥ የምድርም ሕዝብ እጅ ትንቀጠቀጣለች፤ እንደ መንገዳቸውም መጠን አደርግባቸዋለሁ፥ በፍርዳቸውም መጠን እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።