ምዕራፍ 2።

1፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእግርህ ቁም እኔም እናገርሃለሁ አለኝ።

2፤ በተናገረኝም ጊዜ መንፈስ ገባብኝ በእግሬም አቆመኝ፥ የሚናገረኝንም ሰማሁ።

3፤ እርሱም እንዲህ አለኝ። የሰው ልጅ ሆይ፥ በእኔ ላይ ወደ ዐመፁ ወደ ዓመፀኞች ሰዎች ወደ እስራኤል ልጆች እልክሃለሁ። እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐመፁብኝ።

4፤ እነርሱ ፊታቸው የተጨማተረ ልባቸውም የደነደነ ልጆች ናቸው። እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው።

5፤ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ነቢይ በመካከላቸው እንዳለ ያውቃሉ።

6፤ አንተ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ኵርንችትና እሾህ ከአንተ ጋር ቢኖሩም፥ አንተም በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም፥ አትፍራቸው፥ ቃላቸውንም አትፍራ፤ አንተ ቃላቸውን አትፍራ፥ ከፊታቸውም የተነሣ አትደንግጥ፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና።

7፤ እነርሱ ዓመፀኛ ቤት ናቸውና ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ቃሌን ትነግራቸዋለህ።

8፤ አንተ ግን፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ የምነግርህን ስማ፤ እንደዚያ እንደ ዓመፀኛው ቤት ዓመፀኛ አትሁን፤ አፍህን ክፈት የምሰጥህንም ብላ።

9፤ ባየሁም ጊዜ፥ እነሆ፥ እጅ ወደ እኔ ተዘርግታ ነበር፤ እነሆም፥ የመጽሐፍ ጥቅልል ነበረባት።

10፤ በፊቴም ዘረጋው፥ በውስጥና በውጭም ተጽፎበት ነበር፤ ልቅሶና ኀዘን ዋይታም ተጽፎበት ነበር።