ምዕራፍ 39።

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በመቅደሱ ለማገልገል ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም በብልሃት የተሠራ ልብስ፥ ለአሮንም የተቀደሰውን ልብስ አደረጉ።

2፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ኤፉዱን ከወርቅ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገ።

3፤ ወርቁንም ቀጥቅጠው እንደ ቅጠል ስስ አድርገው እንደ ፈትል ቈረጡ። ብልህ ሠራተኛም እንደሚሠራ ሰማያዊ ሐምራዊም ቀይም ግምጃ የተፈተለም ጥሩ በፍታ ከእርሱ ጠለፉ።

4፤ ሁለቱ ወገን እንዲጋጠም በሁለቱ ጫንቃዎች ላይ የሚጋጠም ልብስ አደረጉት።

5፤ በላዩም መታጠቂያ ሆኖ በብልሃት የተጠለፈው የኤፉዱ ቋድ እንደ እርሱ ከእርሱም ጋር አንድ ነበረ፤ ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊ ከቀይ ግምጃም ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የተሠራ ነበረ።

6፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ በወርቅ ፈርጥ የተያዙ የመረግድ ድንጋዮች ሠርተው እንደ ማኅተም ቅርጽ የእስራኤልን ልጆች ስም ቀረጹባቸው።

7፤ ለእስራኤል ልጆች የመታሰቢያ ድንጋዮች ይሆኑ ዘንድ በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ አደረጋቸው።

8፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የደረቱን ኪስ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ እንደ ኤፉዱ አሠራር ከወርቅና ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ አደረገው።

9፤ አራት ማዕዘንም ነበረ፤ የደረቱን ኪስም ድርብ አደረጉ፤ ርዝመቱ ስንዝር፥ ወርዱም ስንዝር፥ ድርብም ነበረ።

10፤ ዕንቍዎቹንም በአራት ተራ አደረጉበት፤ በፊተኛውም ተራ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፤

11፤ በሁለተኛውም ተራ በሉር፥ ሰንፔር፥ አልማዝ፤

12፤ በሦስተኛውም ተራ ያክንት፥ ኬልቄዶን፥ አሜቴስጢኖስ፤

13፤ በአራተኛውም ተራ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ተደረጉ።

14፤ የዕንቍዎችም ድንጋዮች እንደ አሥራ ሁለቱ እንደ እስራኤል ልጆች ስሞች ነበሩ፤ በየስማቸውም ማተሚያ እንደሚቀረጽ ተቀረጹ፥ ስለ አሥራ ሁለቱም ነገዶች ነበሩ።

15፤ ለደረቱ ኪስም የተጐነጐኑትን ድሪዎች እንደ ገመድ አድርገው ከጥሩ ወርቅ ሠሩ።

16፤ ሁለትም የወርቅ ፈርጦች፥ ሁለትም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፤ ሁለቱንም ቀለበቶች በደረቱ ኪስ በሁለቱ ወገን አደረጉ።

17፤ ሁለቱንም የተጐነጐኑትን የወርቅ ድሪዎች በደረቱ ኪስ ወገኖች ወዳሉት ወደ ሁለቱ ቀለበቶች አገቡ።

18፤ የሁለቱንም ድሪዎች ጫፎች በሁለቱ ፈርጦች ውስጥ አግብተው በኤፉዱ ጫንቃዎች ላይ በፊታቸው አደረጉ።

19፤ ሁለቱንም የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ እነርሱንም በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው በደረቱ ኪስ በሁለት ጫፎቹ ላይ አደረጉአቸው።

20፤ ደግሞም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠሩ፥ በኤፉዱም ፊት፥ ከጫንቃዎች በታች፥ በብልሃት ከተጠለፈ ከኤፉዱ ቋድ በላይ፥ በመያዣው አጠገብ አደረጉአቸው።

21፤ የደረቱ ኪስ በብልሃት ከተጠለፈው ከኤፉዱ ቋድ በላይ እንዲሆን፥ ከኤፉዱም እንዳይለይ የደረቱን ኪስ ከቀለበቶቹ ጋር ወደ ኤፉዱ ቀለበቶች በሰማያዊ ፈትል አሰሩት።

22፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ የኤፉዱን ቀሚስ ሞላውን በሸማኔ ሥራ ሰማያዊ አደረገው።

23፤ በቀሚሱም መካከል አንገትጌ ነበረ፤ እንዳይቀደድም እንደ ጥሩር የተሠራ ጥልፍ በአንገትጌው ዙሪያ ነበረ።

24፤ በቀሚሱም ታችኛ ዘርፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ፥ ከተፈተለ በፍታም ሮማኖች አደረጉ።

25፤ ከጥሩ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፥ ሻኵራዎቹንም ከሮማኖች መካከል በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ አደረጉ።

26፤ በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያ ሻኵራንና ሮማንን፥ ሻኵራንና ሮማንን ለማገልገል አደረጉ።

27፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ እንደ ሸማኔ ሥራ ከጥሩ በፍታ ለአሮንና ለልጆቹ ሸሚዞችን፥

28፤ ከጥሩ በፍታም መጠምጠሚያውን፥ ከጥሩ በፍታም መልካሞቹን ቆቦች፥ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ የእግር ሱሪዎችን፥

29፤ ከተፈተለም ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊም ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ በጥልፍ አሠራር የተሠራ መታጠቂያውን አደረጉ።

30፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው፥ ከጥሩ ወርቅ የተቀደሰውን የአክሊል ምልክት ሠሩ፤ በእርሱም እንደ ማኅተም ቅርጽ አድርገው። ቅድስና ለእግዚአብሔር የሚል ጻፉበት።

31፤ በመጠምጠሚያውም ላይ ያንጠለጥሉት ዘንድ ሰማያዊውን ፈትል አሰሩበት።

32፤ እንዲሁም የመገናኛው ድንኳን የማደሪያው ሥራ ሁሉ ተጨረሰ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሁሉ የእስራኤል ልጆች አደረጉ፤ እንዲሁ አደረጉ።

33፤ ማደሪያውንም፥ ድንኳኑንም፥ ዕቃውንም ሁሉ ወደ ሙሴ አመጡ፤ መያዣዎቹን፥ ሳንቆቹን፥ መወርወሪያዎቹን፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፤

34፤ ከቀይ ከአውራ በግ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ ከአቆስጣ ቁርበትም የተሠራ መደረቢያ፥ የሚሸፍነውንም መጋረጃ፤

35፤ የምስክሩንም ታቦት፥ መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም፤

36፤ ገበታውንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የገጹንም ኅብስት፤

37፤ ጥሩውንም መቅረዝ፥ መብራቶቹንም፥ በተራ የሚሆኑትንም ቀንዲሎች፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመብራቱንም ዘይት፤

38፤ የወርቁንም መሠዊያ፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ የድንኳኑንም ደጃፍ መጋረጃ፤

39፤ የናሱንም መሠዊያ፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም መቀመጫውንም፤

40፤ የአደባባዩንም መጋረጆች፥ ምሰሶቹንም፥ እግሮቹንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፥ አውታሮቹንም፥ ካስማዎቹንም፥ ለመገናኛው ድንኳን ለማደሪያው ማገልገያ የሚሆኑን ዕቃዎች ሁሉ፤

41፤ በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነትም ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች አመጡ።

42፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ ሁሉ እንዲሁ የእስራኤል ልጆች ሥራውን ሁሉ ሠሩ።

43፤ ሙሴም ሥራውን ሁሉ አየ፥ እነሆም አድርገውት ነበር፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንዲሁ አድርገውት ነበር፤ ሙሴም ባረካቸው።