ምዕራፍ 1።

1፤ በአርጤክስስም ዘመን እንዲህ ሆነ፤ ይህም አርጤክስስ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በመቶ ሀያ ሰባት አገሮች ላይ ነገሠ።

2፤ በዚያም ዘመን ንጉሡ አርጤክስስ በሱሳ ግንብ በነበረው በመንግሥቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳለ፥

3፤ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ለባለምዋሎቹና ለአገልጋዮቹ ሁሉ ግብዣ አደረገ፤ የፋርስና የሜዶን ታላላቆች ሁሉ፥ የየአገሩ አዛውንትና ሹማምት፥ በፊቱ ነበሩ፤

4፤ የከበረውንም የመንግሥቱን ሀብት፥ የታላቁንም የግርማዊነቱን ክብር መቶ ሰማንያ ቀን ያህል አሳያቸው።

5፤ ይህም ቀን በተፈጸመ ጊዜ በሱሳ ግንብ ውስጥ ለተገኙት ሕዝብ ሁሉ ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ንጉሡ በንጉሡ ቤት አታክልት ውስጥ ባለው አደባባይ ሰባት ቀን ግብዣ አደረገ።

6፤ ነጭ፥ አረንጓዴ፥ ሰማያዊም መጋረጆች ከጥሩ በፍታና ከሐምራዊ ግምጃ በተሠራ ገመድ፥ በብር ቀለበትና በዕብነ በረድ አዕማድ ላይ ተዘርግተው ነበር፤ አልጋዎቹም ከወርቅና ከብር ተሠርተው በቀይና በነጭ በብጫና በጥቁር ዕብነ በረድ ወለል ላይ ነበሩ።

7፤ መጠጡም በልዩ ልዩ በወርቅ ዕቃ ይታደል ነበር፤ የንጉሡም የወይን ጠጅ እንደ ንጉሡ ለጋስነት መጠን እጅግ ብዙ ነበረ።

8፤ ንጉሡም እንደ ሰው ሁሉ ፈቃድ ያደርጉ ዘንድ ለቤቱ አዛዦች ሁሉ አዝዞ ነበርና መጠጡ እንደ ወግ አልነበረም።

9፤ ንግሥቲቱም አስጢን በንጉሡ በአርጤክስስ ቤተ መንግሥት ለሴቶች ግብዣ አደረገች።

10፤11፤ በሰባተኛውም ቀን ንጉሡ አርጤክስስ የወይን ጠጅ ጠጥቶ ደስ ባለው ጊዜ፥ ንግሥቲቱ አስጢን መልከ መልካም ነበረችና ውበትዋ ለአሕዛብና ለአለቆች እንዲታይ የመንግሥቱን ዘውድ ጭነው ወደ ንጉሡ ፊት ያመጡአት ዘንድ በፊቱ የሚያገለግሉትን ሰባቱን ጃንደረቦች ምሁማንን፥ ባዛንን፥ ሐርቦናን፥ ገበታን፥ ዘቶልታን፥ ዜታርን፥ ከርከስን አዘዛቸው።

12፤ ነገር ግን ንግሥቲቱ አስጢን በጃንደረቦቹ እጅ በላከው በንጉሡ ትእዛዝ ትመጣ ዘንድ እንቢ አለች፤ ንጉሡም እጅግ ተቈጣ፥ በቍጣውም ተናደደ።

13፤ ሕግንና ፍርድን በሚያውቁ ሁሉ ፊት የንጉሡ ወግ እንዲህ ነበረና ንጉሡ የዘመኑን ነገር የሚያውቁትን ጥበበኞችን፥

14፤ በመንግሥቱም ቀዳሚዎች ሆነው የሚቀመጡ የንጉሡ ባለምዋሎች ሰባቱ የፋርስና የሜዶን መሳፍንት አርቄስዮስ፥ ሼታር፥ አድማታ፥ ተርሺሽ፥ ሜሬስ፥ ማሌሴዓር፥ ምሙካን በአጠገቡ ሳሉ።

15፤ በጃንደረቦች እጅ የተላከባትን የንጉሡን የአርጤክስስን ትእዛዝ ስላላደረገች በንግሥቲቱ በአስጢን ላይ እንደ ሕጉ የምናደርገው ምንድር ነው? አላቸው።

16፤ ምሙካንም በንጉሡና በአዛውንቱ ፊት እንዲህ አለ። ንግሥቲቱ አስጢን አዛውንቱን ሁሉና በንጉሡ በአርጤክስስ አገር ያሉትን አሕዛብ ሁሉ በድላለች እንጂ ንጉሡን ብቻ የበደለች አይደለችም።

17፤ ይህ የንግሥቲቱ ነገር ወደ ሴቶች ሁሉ ይደርሳልና። ንጉሡ አርጤክስስ ንግሥቲቱ አስጢን ወደ እርሱ ትገባ ዘንድ አዘዘ፥ እርስዋ ግን አልገባችም ተብሎ በተነገረ ጊዜ ባሎቻቸው በዓይናቸው ዘንድ የተናቁ ይሆናሉ።

18፤ ዛሬም የንግሥቲቱን ነገር የሰሙት የፋርስና የሜዶን ወይዛዝር እንዲህና እንዲህ ብለው ለንጉሡ አዛውንት ሁሉ ይናገራሉ፥ ንቀትና ቍጣም ይበዛል።

19፤ ንጉሡም ቢፈቅድ፥ አስጢን ወደ ንጉሡ ወደ አርጤክስስ ፊት ከእንግዲህ ወዲህ እንዳትገባ የንጉሡ ትእዛዝ ከእርሱ ይውጣ፥ እንዳይፈርስም በፋርስና በሜዶን ሕግ ይጻፍ፤ ንጉሡም ንግሥትነትዋን ከእርስዋ ለተሻለችው ለሌላይቱ ይስጥ።

20፤ የንጉሡም ትእዛዝ በሰፊው መንግሥቱ ሁሉ በተነገረ ጊዜ ሴቶች ሁሉ ባሎቻቸውን ታላቁንም ታናሹንም ያከብራሉ።

21፤ ይህም ምክር ንጉሡንና አዛውንቱን ደስ አሰኛቸው፤ ንጉሡም እንደ ምሙካን ቃል አደረገ።

22፤ ሰው ሁሉ በቤቱ አለቃ ይሁን፤ በሕዝቡም ቋንቋ ይናገር ብሎ ለአገሩ ሁሉ እንደ ጽሕፈቱ ለሕዝቡም ሁሉ እንደ ቋንቋው ደብዳቤዎችን ወደ ንጉሡ አገሮች ሁሉ ሰደደ።