ምዕራፍ 3።

1፤ ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።

2፤ ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፤

3፤ ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤

4፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፤

5፤ ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤

6፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤

7፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤

8፤ ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው።

9፤ ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድር ነው?

10፤ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ።

11፤ ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው።

12፤ ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ።

13፤ ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።

14፤ እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር አወቅሁ፤ ሊጨመርበት ወይም ከእርሱ ሊጐድል አይቻልም፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ።

15፤ አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፤ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።

16፤ ደግሞም ከፀሐይ በታች በፍርድ ስፍራ ኃጢአት፥ በጽድቅም ስፍራ ኃጢአት እንዳለ አየሁ።

17፤ እኔም በልቤ። በዚያ ለነገር ሁሉና ለሥራ ሁሉ ጊዜ አለውና በጻድቅና በኃጢአተኛ ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል አልሁ።

18፤ እኔ በልቤ ስለ ሰው ልጆች። እንደ እንስሳ መሆናቸውን እንዲያዩ እግዚአብሔር ይፈትናቸዋል አልሁ።

19፤ የሰው ልጆችና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው፤ ድርሻቸውም ትክክል ነው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፤ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም።

20፤ ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል።

21፤ የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣ የእንስሳም ነፍስ ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው?

22፤ ያም እድል ፈንታው ነውና ሰው በሥራው ደስ ከሚለው በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለው አየሁ፤ ከእርሱ በኋላስ የሚሆነውን ያይ ዘንድ የሚያመጣው ማን ነው?