ምዕራፍ 24።

1፤ ሰው ሴትን ወስዶ ቢያገባ፥ የእፍረት ነገር ስላገኘባት በእርሱ ዘንድ ሞገስ ባታገኝ፥ የፍችዋን ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ይስጣት፥ ከቤቱም ይስደዳት።

2፤ ከቤቱም ከወጣች በኋላ ሌላ ወንድ ብታገባ፥

3፤ ሁለተኛውም ባል ቢጠላት፥ የፍችዋንም ጽሕፈት ጽፎ በእጅዋ ቢሰጣት፥ ከቤቱም ቢሰድዳት፥ ወይም ሚስት አድርጎ ያገባት ሁለተኛው ባልዋ ቢሞት፥

4፤ የሰደዳት የቀድሞ ባልዋ ከረከሰች በኋላ ደግሞ ያገባት ዘንድ አይገባውም፤ ያ በእግዚአብሔር የተጠላ ነው፤ አምላክህም እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር አታርክስ።

5፤ አዲስ ሚስትም ያገባ ሰው ወደ ጦርነት አይሂድ፥ ነገርም አይጫኑበት፤ ነገር ግን አንድ ዓመት በቤቱ በፈቃዱ ይቀመጥ፥ የወሰዳትንም ሚስቱን ደስ ያሰኛት።

6፤ የሰውን ነፍስ እንደ መውሰድ ነውና ወፍጮ ወይም መጅ ስለ መያዣ ማንም አይውሰድ።

7፤ ማንም ሰው ከእስራኤል ልጆች ከወንድሞቹ አንዱን ሰርቆ እንደ ባሪያ ሲያደርግበት ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፥ ያ ሌባ ይሙት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ።

8፤ በለምጽ ደዌ ሌዋውያን ካህናት ያስተማሩህን ሁሉ ፈጽመህ እንድትጠብቅ እንድታደርግም ተጠንቀቅ፤ እኔ ያዘዝኋቸውን እንዲሁ ታደርግ ዘንድ ጠብቅ።

9፤ አምላክህ እግዚአብሔር ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ በመንገድ ሳላችሁ በማርያም ላይ ያደረገውን አስብ።

10፤ ለባልንጀራህ ባበደርኸው ጊዜ መያዣውን ልትወስድ ወደ ቤቱ አትግባ።

11፤ አንተ በውጭ ቁም ያበደርኸውም ሰው መያዣውን ያውጣልህ።

12፤ ያም ሰው ድሃ ቢሆን መያዣውን በአንተ ዘንድ አታሳድር።

13፤ ለብሶት እንዲተኛ እንዲባርክህም ፀሐይ ሳይገባ መያዣውን ፈጽመህ መልስለት፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ጽድቅ ይሆንልሃል

14፤ ድሀና ችግረኛ የሆነውን ምንደኛ፥ ከወንድሞችህ ወይም በምድርህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚቀመጡት መጻተኞች ቢሆን፥ አታስጨንቀው።

15፤ ድሀ ነውና፥ ነፍሱም ጠንክራ ትፈልገዋለችና ወደ እግዚአብሔር እንዳይጮኽብህ ኃጢአትም እንዳይሆንብህ ደመወዙን ፀሐይ ሳይገባ በቀኑ ስጠው።

16፤ አባቶች ስለ ልጆች አይገደሉ፥ ልጆችም ስለ አባቶች አይገደሉ፤ ነገር ግን ሁሉ እያንዳንዱ በኃጢአቱ ይገደል።

17፤ የመጻተኛውንና የድሀ አደጉን ፍርድ አታጣምምባቸው፤ የመበለቲቱን ልብስ ለመያዣ አትውሰድባት።

18፤ አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ፥ አምላክህም እግዚአብሔር ከዚያ እንዳዳነህ አስብ፤ ስለዚህ ይህን ነገር ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ።

19፤ የእርሻህን መከር ባጨድህ ጊዜ ነዶም ረስተህ በእርሻህ ብታስቀር፥ ትወስደው ዘንድ አትመለስ፤ አምላክህ እግዚአብሔር በእጅህ ሥራ ሁሉ እንዲባርክህ፥ ለመጻተኛና ለድሃ አደግ ለመበለትም ተወው።

20፤ የወይራህን ፍሬ ባረገፍህ ጊዜ ከቅርንጫፎቹ ላይ ማርገፉን ለማጣራት አትመለስ፤ ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም ይሁን።

21፤ የወይንህን ፍሬ በቈረጥህ ጊዜ ቃርሚያውን አትልቀመው፤ ለመጻተኛና ለድሀ አደግ ለመበለትም ይሁን።

22፤ አንተም በግብፅ አገር ባሪያ እንደ ነበርህ አስብ፤ ስለዚህ ይህን ታደርግ ዘንድ አዝዤሃለሁ።