ምዕራፍ 20።

1፤ ጠላቶችህን ለመውጋት በወጣህ ጊዜ፥ ፈረሶችንና ሰረገሎችን ሕዝቡንም ከአንተ ይልቅ በዝተው ባየህ ጊዜ፥ ከግብፅ አገር ያወጣህ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና አትፍራቸው።

2፤ ወደ ሰልፍም በቀረባችሁ ጊዜ ካህኑ ይቅረብ ለሕዝቡም እንዲህ ብሎ ይንገራቸው።

3፤ እስራኤል ሆይ፥ ስሙ፤ ዛሬ ጠላቶቻችሁን ለመውጋት ትቀርባላችሁ፤ ልባችሁ አይታወክ፥ አትፍሩ፥ አትንቀጥቀጡ፥ በፊታቸውም አትደንግጡ፤

4፤ ከእናንተ ጋር የሚሄድ፥ ያድናችሁም ዘንድ ጠላቶቻችሁን ስለ እናንተ የሚወጋ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነውና።

5፤ አለቆችም ለሕዝቡ እንዲህ ብለው ይናገሩ። አዲስ ቤት ሠርቶ ያላስመረቀ ሰው ቢኖር በሰልፍ እንዳይሞት ሌላም ሰው እንዳያስመርቀው ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ።

6፤ ወይንም ተክሎ ፍሬውንም ያልበላ ሰው ቢኖር በሰልፍ እንዳይሞት ሌላም ሰው ፍሬውን እንዳይበላ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ።

7፤ ሚስትም አጭቶ ያላገባትም ሰው ቢኖር በሰልፍ እንዳይሞት ሌላም ሰው እንዳያገባት ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ።

8፤ አለቆቹም ደግሞ ጨምረው። ማንም ፈሪና ድንጉጥ ሰው ቢሆን እርሱ ፈርቶ የወንድሞቹን ልብ ደግሞ እንዳያስፈራ ወደ ቤቱ ተመልሶ ይሂድ ብለው ለሕዝቡ ይናገሩ።

9፤ አለቆቹም ለሕዝቡ ነግረው በጨረሱ ጊዜ በየጭፍራው በሕዝቡ ላይ የጦር አለቆችን ይሹሙ።

10፤ ለመዋጋት ወደ አንዲት ከተማ በደረስህ ጊዜ አስቀድመህ በዕርቅ ቃል ጥራቸው።

11፤ የዕርቅ ቃልም ቢመልሱልህ ደጅም ቢከፍቱልህ፥ በከተማ ውስጥ ያለው ሕዝብ ሁሉ ይገብሩልህ ያገልግሉህም።

12፤ የዕርቅ ቃልም ባይመልሱልህ ከአንተም ጋር መዋጋት ቢወድዱ፥ አንተ ከተማይቱን ትከብባለህ ታስጨንቃትማለህ፤

13፤ አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጣት ጊዜ፥ በእርስዋ ያሉትን ወንዶች ሁሉ በሰይፍ ስለት ትገድላቸዋለህ፤

14፤ ነገር ግን ሴቶቹንና ሕፃናትን እንስሶቹንም በከተማይቱም ያለውን ምርኮ ሁሉ በዝብዘህ ለአንተ ትወስዳለህ፤ አምላክህም እግዚአብሔር የሚሰጥህን የጠላቶችህን ምርኮ ትበላለህ።

15፤ የእነዚህ አሕዛብ ከተሞች ባይደሉት ከአንተ እጅግ በራቁት ከተሞች ሁሉ እንዲሁ ታደርጋለህ።

16፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ ከሚሰጥህ ከእነዚህ አሕዛብ ከተሞች ምንም ነፍስ አታድንም።

17፤18፤ ነገር ግን ለአማልክቶቻቸው ያደረጉትን ርኵሰት ሁሉ ታደርጉ ዘንድ እንዳያስተምሩአችሁ፥ በአምላካችሁም በእግዚአብሔር ላይ ኃጢአት እንዳትሠሩ፥ አምላክህ እግዚአብሔር እንዳዘዘህ ኬጢያዊውን አሞራዊውንም ከነዓናዊውንም ፌርዛዊውንም ኤዊያዊውንም ኢያቡሳዊውንም ፈጽመህ ታጠፋቸዋለህ።

19፤ ከተማይቱን ለመውሰድ በመውጋት ብዙ ቀን ከብበህ ባስጨነቅሃት ጊዜ፥ ምሳርህን አንሥተህ ዛፎችዋን አትቍረጥ፤ ከእነርሱ ትበላለህና አትቍረጣቸው፤ ከብበህ የምታጠፋው የምድር ዛፍ ሰው መሆኑ ነውን?

20፤ ለመብል የማይሆኑትን የምታውቃቸውን ዛፎች ታጠፋቸዋለህ፥ ትቈርጣቸውማለህ፤ እስክታሸንፋትም ድረስ በምትዋጋህ ከተማ ላይ ምሽግ ትመሽጋለህ።