ምዕራፍ 12።

1፤ እግዚአብሔርም ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፥ ወደ እርሱም መጥቶ አለው። በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሀ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ።

2፤ ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው።

3፤ ለድሀው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፤ አሳደጋትም፥ ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፤ እንጀራውንም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበር፥ እንደ ልጁም ነበረች።

4፤ ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፤ የዚያንም የድሀውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ።

5፤ ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን። ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው።

6፤ ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ አለው።

7፤ ናታንም ዳዊትን አለው። ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤

8፤ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር።

9፤ አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል።

10፤ ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም።

11፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፤ ሚስቶችህንም በዓይንህ ፊት እወስዳለሁ፥ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፥ በዚህችም ፀሐይ ዓይን ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል።

12፤ አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ።

13፤ ዳዊትም ናታንን። እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን። እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትም።

14፤ ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል አለው።

15፤ ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈ፥ እጅግም ታምሞ ነበር።

16፤ ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፤ ዳዊትም ጾመ፥ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ።

17፤ የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፥ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም።

18፤ በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ባሪያዎች። ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፤ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በነፍሱ ክፉ ያደርጋል ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ።

19፤ ዳዊትም ባሪያዎቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ አወቀ፤ ዳዊትም ባሪያዎቹን። ሕፃኑ ሞቶአል? አላቸው። እነርሱም። ሞቶአል አሉት።

20፤ ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፥ ተቀባም፥ ልብሱንም ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ። እንጀራ አምጡልኝ አለ፤ በፊቱም አቀረቡለት፥ በላም።

21፤ ባሪያዎቹም። ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፤ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት።

22፤ እርሱም። ሕፃኑ ሕያው ሳለ። እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ አለቅሰሁም።

23፤ አሁን ግን ሞቶአል፤ የምጾመው ስለ ምንድር ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ።

24፤ ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፥ ወደ እርስዋም ገባ፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ፤ ወንድ ልጅም ወለደች፥ ስሙንም ሰሎሞን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ወደደው፤

25፤ ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔር ይዲድያ ብሎ ጠራው።

26፤ ኢዮአብም የአሞንን ልጆች ከተማ ረባትን ወጋ፥ የውኃውንም ከተማ ያዘ።

27፤ ኢዮአብም ወደ ዳዊት። ረባትን ወግቻለሁ፥ የውኃውንም ከተማ ይዤአለሁ።

28፤ አሁንም ከተማይቱን እንዳልይዝ፥ በስሜም እንዳትጠራ፥ የቀረውን ሕዝብ ሰብስብ፥ ከተማይቱንም ከብበህ ያዝ ብሎ መልእክተኞችን ላከ።

29፤ ዳዊትም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ረባት ሄደ፥ ወግቶም ያዛት።

30፤ የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበር፥ ክቡር ዕንቍም ነበረበት፤ ዳዊትም በራሱ ላይ አደረገው። ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ።

31፤ በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቈፈሪያና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፤ የሸክላ ጡብም እንዲያቃጥሉ አደረጋቸው፤ በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲህ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።