ምዕራፍ 10።

1፤ ከዚህ በኋላ የአሞን ልጆች ንጉሥ ሞተ፥ ልጁም ሐኖን በፋንታው ነገሠ።

2፤ ዳዊትም። አባቱ ወረታ እንዳደረገልኝ እኔ ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ቸርነት አደርጋለሁ አለ። ዳዊትም አባቱ ስለ ሞተ ሊያጽናናው ባሪያዎቹን ላከ፤ የዳዊትም ባሪያዎች ወደ አሞን ልጆች አገር መጡ።

3፤ የአሞንም ልጆች አለቆች ጌታቸውን ሐኖንን። ዳዊት አባትህን አክብሮ ሊያጽናናህ ባሪያዎቹን ወደ አንተ የላከ ይመስልሃልን? ዳዊትስ ከተማይቱን ለመመርመርና ለመሰለል ለማጥፋትም ባሪያዎቹን የላከ አይደለምን? አሉት።

4፤ ሐኖንም የዳዊትን ባሪያዎች ወስዶ የጢማቸውን ገሚስ ላጨ፥ ልብሳቸውንም እስከ ወገባቸው ድረስ ከሁለት ቀድዶ ሰደዳቸው።

5፤ ዳዊትም ያን በሰማ ጊዜ ሰዎቹ እጅግ አፍረው ነበሩና ተቀባዮች ላከ። ንጉሡም። ጢማችሁ እስኪያድግ ድረስ በኢያሪኮ ተቀመጡ፥ ከዚያም በኋላ ተመለሱ አላቸው።

6፤ የአሞን ልጆች በዳዊት ዘንድ እንደተጠሉ ባዩ ጊዜ፥ የአሞን ልጆች ልከው ከሶርያውያን ከቤትሮዖብና ከሱባ ሀያ ሺህ እግረኞች፥ ከመዓካ ንጉሥም አንድ ሺህ ሰዎች፥ ከጦብም አሥራ ሁለት ሺህ ሰዎች ቀጠሩ።

7፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ኢዮአብንና የኃያላኑን ሠራዊት ሁሉ ላከ።

8፤ የአሞንም ልጆች ወጥተው በበሩ መግቢያ ፊት ለፊት ተሰለፉ፤ የሱባና የረአብ ሶርያውያን፥ የጦብና የመዓካም ሰዎች ለብቻቸው በሰፊ ሜዳ ላይ ነበሩ።

9፤ ኢዮአብም በፊትና በኋላ ሰልፍ እንደ ከበበው ባየ ጊዜ ከእስራኤል ምርጥ ምርጦቹን ሁሉ መረጠ፥ በሶርያውያንም ፊት ለሰልፍ አኖራቸው።

10፤ የቀረውንም ሕዝብ በወንድሙ በአቢሳ እጅ አድርጎ በአሞን ልጆች ፊት ለሰልፍ አኖራቸው።

11፤ ሶርያውያን ቢበረቱብኝ ትረዳኛለህ፤ የአሞን ልጆች ቢበረቱብህ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ።

12፤ አይዞህ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችንም ከተሞች እንበርታ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ አለ።

13፤ ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ከሶርያውያን ጋር ሊዋጉ ቀረቡ፥ እነርሱም ከፊቱ ሸሹ።

14፤ የአሞንም ልጆች ሶርያውያን እንደ ሸሹ ባዩ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ከአቢሳ ፊት ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ገቡ፤ ኢዮአብም ከአሞን ልጆች ዘንድ ተመልሶ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ።

15፤ ሶርያውያንም በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ በአንድነት ተሰበሰቡ።

16፤ አድርአዛርም ልኮ በወንዝ ማዶ የነበሩትን ሶርያውያን፥ አመጣ፤ ወደ ኤላምም መጡ፥ የአድርአዛርም ሠራዊት አለቃ ሶባክ በፊታቸው ነበረ።

17፤ ዳዊትም በሰማ ጊዜ እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ ዮርዳኖስንም ተሻግሮ ወደኤላም መጣ፤ ሶርያውያንም በዳዊት ፊት ተሰልፈው ከእርሱ ጋር ተዋጉ።

18፤ ሶርያውያንም ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ከሶርያውያን ሰባት መቶ ሰረገለኞች አርባ ሺህም ፈረሰኞች ገደለ፤ የሠራዊቱንም አለቃ ሶባክን መታ፥ እርሱም በዚያ ሞተ።

19፤ ለአድርአዛርም የሚገብሩ ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል ፊት እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ጋር ታረቁ፥ ገበሩላቸውም። ሶርያውያንም ከዚያ ወዲያ የአሞንን ልጆች ይረዱ ዘንድ ፈሩ።