ምዕራፍ 2።

1፤ ከዚያም በኋላ ዳዊት። ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም። ውጣ አለው። ዳዊትም። ወዴት ልውጣ? አለ። እርሱም። ወደ ኬብሮን ውጣ አለው።

2፤ ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ።

3፤ ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎችና ቤተ ሰባቸውን ሁሉ አመጣ፤ በኬብሮንም ከተሞች ተቀመጡ።

4፤ የይሁዳም ሰዎች መጥተው በይሁዳ ቤት ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን በዚያ ቀቡት። ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ናቸው ብለው ለዳዊት ነገሩት።

5፤ ዳዊትም ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው። እናንተ ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፥ ቀብራችሁትማልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ።

6፤ አሁንም እግዚአብሔር ቸርነትንና እውነትን ያድርግላችሁ፤ ይህንም ነገር አድርጋችኋልና እኔ ደግሞ ይህን ቸርነት እመልስላችኋለሁ።

7፤ አሁንም ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና እጃችሁ ትጽና፥ እናንተም ጨክኑ፤ ዳግም የይሁዳ ቤት በእነርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብተውኛል።

8፤ የሳኦልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደመሃናይም አሻገረው፤

9፤ በገለዓድና በአሹራውያን በኢይዝራኤልም በኤፍሬምም በብንያምም በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሠው።

10፤ የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴም በእስራኤል ላይ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ነገሠ፤ ነገር ግን የይሁዳ ቤት ዳዊትን ተከተለ።

11፤ ዳዊትም በይሁዳ ቤት ነግሦ በኬብሮን የተቀመጠበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ።

12፤ የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ባሪያዎች ከመሃናይም ወደ ገባዖን ወጡ።

13፤ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ባሪያዎች ወጥተው በገባዖን ውኃ መቆሚያ አጠገብ ተገናኙአቸው፤ በውኃውም መቆሚያ በአንዱ ወገን እነዚህ፥ በሌላውም ወገን እነዚያ ሆነው ተቀመጡ።

14፤ አበኔርም ኢዮአብን። ጕልማሶች ይነሡ፥ በፊታችንም ይቈራቈሱ አለው፤ ኢዮአብም። ይነሡ አለ።

15፤ ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ አስራ ሁለት፥ ከዳዊትም ባሪያዎች አሥራ ሁለት ተቈጥረው ተነሡ።

16፤ ሁሉም እያንዳንዱ የወደረኛውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በወደረኛው ጎን ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። የዚያም ስፍራ ስም የስለታም ሰይፍ እርሻ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም በገባዖን ነው።

17፤ በዚያም ቀን ጽኑ ሰልፍ ሆነ፤ በዳዊትም ባሪያዎች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ።

18፤ በዚያም ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብና አቢሳ አሣሄልም ነበሩ፤ አሣሄልም እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ።

19፤ አሣሄልም የአበኔርን ፍለጋ ተከታተለ፥ አበኔርንም ከማሳደድ ቀኝና ግራ አላለም።

20፤ አበኔርም ዘወር ብሎ ተመለከተና። አንተ አሣሄል ነህን? አለ። እርሱም። እኔ ነኝ አለ።

21፤ አበኔርም። ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፤ አንድ ጕልማሳ ያዝ፥ መሣርያውንም ውሰድ አለው። አሣሄል ግን እርሱን ከማሳደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ።

22፤ አበኔርም አሣሄልን። ከምድር ጋር እንዳላጣብቅህ እኔን ከማሳደድ ፈቀቅ በል፤ ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ፊቴን አቅኝቼ አይ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? አለው።

23፤ ነገር ግን ከእርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ፤ አበኔርም በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በኋላው ወጣ፥ በዚያም ስፍራ ወድቆ ሞተ። አሣሄልም ወድቆ በሞተበቱ ስፍራ የሚያልፍ ሁሉ ይቆም ነበር።

24፤ ኢዮአብና አቢሳም አበኔርን አሳደዱ፤ በገባዖንም ምድረ በዳ መንገድ በጋይ ፊት ለፊት እስካለው እስከ አማ ኮረብታ ድረስ በወጡ ጊዜ ፀሐይ ጠለቀች።

25፤ የብንያምም ልጆች ወደ አበኔር ተሰበሰቡ፥ በአንድነትም ሆኑ፥ በኮረብታም ራስ ላይ ቆሙ።

26፤ አበኔርም ወደ ኢዮአብ ጮኸ። ሰይፍ በውኑ እስከ ዘላለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደ ሆነ አታውቅምን? ሕዝቡ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን የማትናገር እስከ መቼ ነው? አለው።

27፤ ኢዮአብም። ሕያው እግዚአብሔርን! ባትናገር ኖሮ ሕዝቡ በጥዋት ወጥተው በሄዱ ነበር፥ ወንድሞቻቸውንም ማሳደድ በተዉ ነበር አለ።

28፤ ኢዮአብም ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም ሁሉ ቆመ፥ ከዚያም በኋላ እስራኤልን አላሳደደም፥ ሰልፍም አላደረገም።

29፤ አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ዓረባ እያለፉ ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ ቢትሮንንም ሁሉ ካለፉ በኋላ ወደ መሃናይም መጡ።

30፤ ኢዮአብም አበኔርን ከማሳደድ ተመለሰ፤ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበ፥ ከዳዊትም ባሪያዎች ከአሣሄል ሌላ አሥራ ዘጠኝ ሰዎች ጐደሉ።

31፤ የዳዊትም ባሪያዎች ከብንያምና ከአበኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ያህል ገደሉ።

32፤ አሣሄልንም አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት፤ ኢዮአብና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ በኬብሮንም አነጉ።