ምዕራፍ 23።

1፤ ንጉሡም ላከ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምንም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰባቸው።

2፤ ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጣ፤ ከእርሱም ጋር የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ፥ ካህናቱና ነቢያቱም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሾቹ ጀምሮ እስከ ታላቆቹ ድረስ ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ።

3፤ ንጉሡም በዓምደ ወርቁ አጠገብ ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ ይሄድ ዘንድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩንም ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ይጠብቅ ዘንድ፥ በዚሁም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸና ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ፤ ሕዝቡም ሁሉ ቃል ኪዳን ገቡ።

4፤ ንጉሡም የካህናቱን አለቃ ኬልቅያስን በሁለተኛውም መዓርግ ያሉትን ካህናትን በረኞቹንም ለባኣልና ለማምለኪያ ዐፀድ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ ከኢየሩሳሌምም ውጭ በቄድሮን ሜዳ አቃጠላቸው፥ አመዱንም ወደ ቤቴል ወሰደው።

5፤ የይሁዳ ነገሥታትም በይሁዳ ከተሞች በነበሩት በኮረብታው መገጃዎች በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ መስገጃዎች ያጥኑ ዘንድ ያኖሩአቸውን የጣዖቱን ካህናት፥ ለበኣልና ለፀሐይ ለጨረቃና ለከዋክብት ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ያጥኑ የነበሩትንም አስወገደ።

6፤ የማምለኪያ ዐፀድንም ጣዖት ከእግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ውጭ ወደ ቄድሮን ፈፋ አወጣው፤ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው፥ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ ትቢያውንም በሕዝብ መቃብር ላይ ጣለው።

7፤ ሴቶቹም ለማምለኪያ ዐፀድ መጋረጃ ይፈትሉባቸው የነበሩትን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሉትን የሰዶማውያንን ቤቶች አፈረሰ።

8፤ ካህናቱንም ሁሉ ከይሁዳ ከተሞች አወጣቸው፤ ከጌባም ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ካህናት ያጥኑበት የነበረውን የኮረብታ መስገጃ ሁሉ ርኩስ አደረገው። በከተማይቱም በር በግራ በኩል በነበረው በከተማይቱ ሹም በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን መስገጃዎች አፈረሰ።

9፤ የኮረብታው መስገጃዎች ካህናት ግን በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ አይመጡም ነበር፤ ብቻ በወንድሞቻቸው መካከል ቂጣ እንጀራ ይበሉ ነበር።

10፤ ማንም ሰው ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት እንዳያሳልፍ በሄኖም ልጆች ሸለቆ የነበረውን ቶፌትን ርኩስ አደረገው።

11፤ የይሁዳም ነገሥታት በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ አጠገብ በከተማው አቅራቢያ በነበረው በጃንደረባው በናታንሜሌክ መኖሪያ አጠገብ ለፀሐይ የሰጡትን ፈረሶች አስወገደ፤ የፀሐይንም ሰረገሎች በእሳት አቃጠለ።

12፤ የይሁዳም ነገሥታት ያሠሩትን በአካዝ ቤት ሰገነት ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች፥ ምናሴም ያሠራውን በእግዚአብሔር ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች ንጉሡ አስፈረሳቸው፥ አደቀቃቸውም፥ ትቢያቸውንም በቄድሮን ፈፋ ጣለ።

13፤ በኢየሩሳሌምም ፊት ለፊት በርኵሰት ተራራ ቀኝ የነበሩትን፥ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን ርኵሰት ለአስታሮት ለሞዓብም ርኵሰት ለካሞሽ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሚልኮም ያሠራቸውን መስገጃዎች ንጉሡ ርኩስ አደረገ።

14፤ ሐውልቶቹንም ሁሉ አደቀቀ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፥ በስፍራቸውም የሙታንን አጥንት ሞላበት።

15፤ ደግሞም በቤቴል የነበረውን መሠዊያ፥ እስራኤልንም ያሳተ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ያሠራውን የኮረብታውን መስገጃ፥ ይህን መሠዊያና መስገጃ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹንም ሰባበረ፥ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ የማምለኪያ ዐፀዱንም አቃጠለው።

16፤ ኢዮስያስም ዘወር ብሎ በተራራው የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ኢዮርብዓምም በበዓል ጊዜ በመሠዊያ አጠገብ ሲቆም እነዚህን ነገሮች የተነባ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ ልኮ ከመቃብሮቹ አጥንቶቹን አስወጣ፥ በመሠዊያውም ላይ አቃጠላቸው አረከሰውም። ዘወርም ብሎ ወደ ተናገረው ወደ እግዚአብሔር ሰው መቃብር ዓይኖቹን አቅንቶ።

17፤ ያ የማየው የመታሰቢያ ምልክት ምንድር ነው? አለ። የዚያችም ከተማ ሰዎች። ከይሁዳ ወጥቶ በቤቴል መሠዊያ ላይ ይህን ያደረግኸውን ነገር የተናገረው የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው ብለው ነገሩት።

18፤ እርሱም። ተዉት፥ ማንም አጥንቱን አያንቀሳቅሰው አለ፤ እነርሱም ከሰማርያ ከወጣው ከነቢዩ አጥንት ጋር አጥንቱን ተዉ።

19፤ በሰማሪያም ከተሞች የነበሩትን፥ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ የእስራኤል ነገሥታት የሠሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ኢዮስያስ አስወገዳቸው፥ በቤቴልም እንዳደረገው ነገር ሁሉ እንዲሁ አደረገባቸው።

20፤ በዚያም የነበሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ካህናት ሁሉ በመሠዊያዎቹ ላይ ገደላቸው፥ የሰዎቹንም አጥንት በመሠዊያዎቹ ላይ አቃጠለ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።

21፤ ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ። በዚህ በቃል ኪዳን መጽሐፍ እንደ ተጻፈው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ፋሲካ አድርጉ ብሎ አዘዛቸው።

22፤ እንደዚህም ያለ ፋሲካ በእስራኤል ላይ ይፈርዱ ከነበሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ አልተፈሰከም።

23፤ ነገር ግን በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተፈሰከ።

24፤ ደግሞም ካህኑ ኬልቅያስ በእግዚአብሔር ቤት ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈውን የሕጉን ቃል ያጸና ዘንድ፥ መናፍስት ጠሪዎቹንና ጠንቋዮቹን ተራፊምንና ጣዖታትንም በይሁዳ አገርና በኢየሩሳሌም የተገኘውን ርኵሰት ሁሉ ኢዮስያስ አስወገደ።

25፤ እንደ ሙሴም ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ በፍጹምም ነፍሱ በፍጹምም ኃይሉ ወደ እግዚአብሔርም የተመለሰ እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ ከእርሱ አስቀድሞ አልነበረም፤ እንደ እርሱም ያለ ንጉሥ ከእርሱ በኋላ አልተነሣም።

26፤ ነገር ግን ምናሴ ስላስቈጣው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከታላቁ ቍጣው ትኵሳት አልተመለሰም።

27፤ እግዚአብሔርም። እስራኤልን እንዳራቅሁት ይሁዳን ከፊቴ አርቀዋላሁ፤ ይህችንም የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና። ስሜ በዚያ ይሆናል ያልሁትን ቤት እጥላለሁ አለ።

28፤ የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን?

29፤ በእርሱም ዘመን የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ ከአሦር ንጉሥ ጋር ሊጋጠም ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወጣ፤ ንጉሡም ኢዮስያስ ከእርሱ ጋር ሊጋጠም ወጣ፤ ፈርዖንም በተገናኘው ጊዜ በመጊዶ ገደለው።

30፤ ከሞተም በኋላ ባሪያዎቹ በሰረገላው አድርገው ከመጊዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፥ በመቃብሩም ቀበሩት። የአገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወሰዱት፥ ቀብተውም በአባቱ ፋንታ አነገሡት።

31፤ ኢዮአክስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ ሦስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። እናቱም አሚጣል ትባል ነበር፥ እርስዋም የልብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።

32፤ አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።

33፤ በኢየሩሳሌምም እንዳይነግሥ ፈርዖን ኒካዑ በሐማት ምድር ባለችው በሪብላ አሰረው፤ በምድሩም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ ፈሰሴ ጣለበት።

34፤ ፈርዖን ኒካዑም የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ አነገሠ፥ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው። ኢዮአክስንም ወስዶ ወደ ግብጽ አፈለሰው፤ በዚያም ሞተ።

35፤ ኢዮአቄምም ብሩንና ወርቁን ለፈርዖን ሰጠው፤ እንደ ፈርዖንም ትእዛዝ ገንዘብ ይሰጥ ዘንድ ምድሩን አስገበረ፤ ለፈርዖን ኒካዑም ይሰጥ ዘንድ ከአገሩ ሕዝብ ሁሉ እንደ ግምጋሜው ብርና ወርቅ አስከፈለ።

36፤ ኢዮአቄምም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አምስት ዓመት ጕልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ዘቢዳ ትባል ነበር፤ እርስዋም የሩማ ሰው የፈዳያ ልጅ ነበረች።

37፤ አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።